“አዲሱ ዓመት የልዩነትን አጥር አፍርሰን የአንድነት ሐውልት ለመትከል የምንተጋበት ዘመን ይሆናል ” አፈጉባዔ አገኘሁ ተሻገር

87

ባሕር ዳር: ጳጉሜን 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ለ2016 የዘመን መለወጫ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም አዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ የሚጸነስበት፤ ካሳለፍነው ችግርና ስኬት በመማር ለተሻለ ለውጥና ለአዲስ ተስፋ ራሳችንን የምናዘጋጅበት ነው ብለዋል፡፡

ቀጣዩ ዓመት እንደሀገር ለድሕነት የዳረጉንን ችግሮች ተሻግረን በፍቅር እጅ ለእጅ ተያይዘን ለአንድ ሀገራዊ አላማ የምንቆምበትና ለተግባራዊነቱም ያለእረፍት የምንሠራበት ይሆናልም ብለዋል።

አሁን ላይ የሕዝቦችን ደኅንነት የሚያውኩ፣ ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ የመሥራት መብትን የሚገድቡና እንደሀገር የብልጽግና ጉዞን ወደኋላ የሚጎትቱ ክስተቶች እንደሚስተዋሉ አንስተዋል፡፡

ለእነዚህ ችግሮች በዋናነት ለረዥም ዘመናት ምላሽ ሳያገኙ ሲንከባለሉ የመጡ የሕዝቦች እኩል የመልማት፣ ፍትሕ የማግኘትና ማንነቴ ይከበርልኝ ጥያቄዎች መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ምክር ቤቱ እነዚህን ጥያቄዎች በቅደም ተከተል ለመመለስ እቅዶ እየተንቀሳቀሰ ነው ያሉት አፈ ጉባዔው÷ ከአዲሱ ዓመት ጀምሮ በተጠናና የሀገር አንድነትን በሚያጸና መልኩ ምላሽ ለመስጠት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል፡፡

አፈጉባዔ አገኘሁ አዲሱ ዓመት አሮጌውን የልዩነት አጥር አፍርሰን አዲስ የአንድነት ሐውልት ለመትከል የምንተጋበት ዘመን ይሆናል ሲሉም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በአዲሱ ዓመት አዲስ ተስፋ እና ራዕይ በመሰነቅ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ፣ ምዕመኑ ተግቶ ሊሠራ ይገባል” የሃይማኖት አባቶች
Next article“መፎካከር ሳይኾን መመካከር ያስፈልገናል” ሐጂ ተዘራ አበበ