የኢትዮጵያን የዘመን አቆጣጠር በሥርዓተ ትምህርቱ በማካተት ትውልዱን ማሳወቅ ይገባል።

108

ባሕር ዳር: ጳጉሜን 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያን የዘመን አቆጣጠር በሥርዓተ ትምህርቱ በማካተት ለትውልዱ ማሳወቅ እንደሚገባ የሃይማኖት መምህራን ገለጹ።

በዋግኽምራ ሀገረስብከት ሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ የጉባዔ ቤት መምህር መዝገበቃል ገብረሕይወት እንደገለጹት፤ በዓለም ላይ የራሳቸው ፊደልና የዘመን አቆጣጠር ካሏቸው ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት።

የኢትዮጵያን የዘመን አቆጣጠር በሚገባ ማስተዋወቅ ይገባል ያሉት መምህር መዝገበቃል፤ የዘመን ቀመሩን የኢትዮጵያ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ በማካተት ትውልዱ ከልጅነት ጀምሮ እየተማሩት እንዲያድጉ ሊደረግ እንደሚገባ አስታውቀዋል።

እንደ መምህር መዝገበቃል ገለጻ፣ የዘመን አቆጣጠሩን ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅና እንዲገለገሉበት ማድረግ የሚቻለው ኢትዮጵያ የራሷን ባህል፣ ትውፊት፣ ሥርዓት እና ማንነት መጠበቅ ስትችል ነው። አንዲት ሀገር ከራሷ የሚተርፈውን ማንኛውም ነገር ለሌሎች ሀገራት ማሳወቅ የምትችለው ከፍ ብላ መታየት ስትጀምር በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በመተጋገዝ የዘመን ቀመሩን ማሳወቅ ተገቢ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ ባለመካተቱ ትውልዱ ከልጅነት ጀምሮ እየተማረ እንዳያድግ፣ ምሁራን ለሌሎች ሀገራት እንዳያሳውቁ እና ኢትዮጵያውያን የሌላ ሀገር ዘመን አቆጣጠር እንዲከተሉ ምክንያት ሆኗል ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ቀመር ከጁሊያንም ሆነ ከጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር በስሌትና በቀመር የተለየ ነው ያሉት መምህር መዝገበቃል፤ የኢትዮጵያ ዘመን መቆጠር የጀመረው ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ሲሆን፤ መነሻው መጽሐፍ ቅዱስ እና ጥንተ ፍጥረት መሆኑን ገልጸዋል።

የጁሊያን ብሎም የጎርጎሮሳውያን የዘመን ቀመሮች መነሻቸው ዕምነትን ሳይሆን ታሪክን ታሳቢ ያደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያውያን ከሌሎች በተለየ አዲስ ዓመታቸውን በወርሃ መስከረም የሚጀምሩ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር የግሪጎሪያን የዘመን ቀመር ከሚጠቀሙ ሀገራት ጋር ከመስከረም እስከ ጥር ወራት በሰባት፤ እንዲሁም ከየካቲት እስከ ነሐሴ በስምንት ዓመት እንደሚለያይ አብራርተዋል።

በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት የወልድያ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ መጋቢጥበባት አክሊለብርሃን ተመስገን በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር መጸሐፍ ቅዱስን እና ጥንተ ፍጥረትን መነሻ ያደረገ ነው።

እንደ መጋቢጥበባት አክሊለብርሃን ገለጻ፣ ኢትዮጵያ የ13 ወር ባለቤት መሆኗ ልዩ ያደርጋታል። ከመስከረም እስከ ነሐሴ ያሉ ወራቶች በ30 ቀናት የተከፈሉና ኢትዮጵያዊ ስምና ስያሜ ያላቸው ናቸው። ጳጉሜን ወር ግን በየዓመቱ አምስት ቀናትን ስትይዝ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ስድስት ቀን እና በየ700 ዓመቱ ሰባት ቀን እንደምትሆን አስረድተዋል።

ኢፕድ እንደዘገበው የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ከሌሎች ሀገራት የሚለይ ሲሆን፤ የዘመን አቆጣጠሩን ጠብቆ ለማስቀጠል፣ ትውልዱን ለማሳወቅ፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን እና ሌሎች ሀገራት እንዲገለገሉበት ለማድረግ በሙያው የሚያገለግሉ በርካታ መምህራንን ማፍራት ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በአዲሱ ዓመት ምክር ቤቶች የሕዝብን ሰላም እና የጋራ ተጠቃሚነት መረጋገጥ ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ ይገባል” አፈጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ
Next article“በአዲሱ ዓመት አዲስ ተስፋ እና ራዕይ በመሰነቅ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ፣ ምዕመኑ ተግቶ ሊሠራ ይገባል” የሃይማኖት አባቶች