
ባሕር ዳር: ጳጉሜ 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ አዲሱን ዓመት አስመልክቶ ለመላው ኢትዮጵያውያን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
አፈጉባኤ ፋንቱ እንዳሉት የምክር ቤቶች ኀላፊነት የሕዝብን ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ የሚችል፣ ዘመኑን የሚመጥን ሕግ ማውጣት እና የሕዝብን ውክልና በተገቢው መንገድ መወጣት ነው፡፡
በአዲሱ ዓመት ምክር ቤቶች የሕዝብን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ሥራ ቅድሚያ ሰጥተው እንደሚሠሩ አፈ ጉባኤዋ ገልጸዋል። አሁን ላይ የታየውን የክልሉን አንጻራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም ለማሸጋገር ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።
ተቋማት ያቀዱትን እቅድ መፈጸማቸውን ሕዝቡን ባሳተፈ መንገድ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ፤ የአማራ ክልል ሕዝብን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ሌላው የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መኾኑንም አንስተዋል።
በተለይም በክልሉ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ጭምር አጋዥ እንዲኾኑ ማድረግ ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራም ነው ያነሱት፡፡
ማኅበረሰቡ በአካባቢው በሚሠሩ ሥራዎች ላይ ከእቅድ ጀምሮ በንቃት እንዲሳተፍ መክረዋል፡፡ በየደረጃው የሚገኙ የሥራ ኀላፊዎችንና ባለሙያዎችን በመደገፍ ለተሻለ ሥራ ማነሳሳት ይገባልም ብለዋል፡፡
ፍላጎትን በኀይል ለመፈጸም መንቀሳቀስ ሕዝብን ማጎሳቆል መኾኑን በመረዳት ችግሮችን በሠለጠነ መንገድ ማቅረብ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት። በየደረጃው የሚገኙ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማትም ለሚቀርቡ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ እንዲሠጡ አሳስበዋል፡፡
የፖለቲካ ድርጅቶች በሀገር ግንባታ እና በትውልድ ማነጽ ሥራ ላይ በጋራ እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
