
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአብሮነት ቀን ‹‹በኅብር የተሠራች ሀገር ›› በሚል መሪ መልእክት እየተከበረ ነው፡፡ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ የአብሮነት ቀንን አስመልክቶ እንዳሉት ተደማጭና የታፈረ ታላቅ ሀገር ለመገንባት የመቻቻልና የአብሮነት ፋይዳው ከፍተኛ ነው፡፡
አባቶቻችን በሀገረ ግንባታ ሂደት ላይ ቋንቋ፣ ባሕል፣ ሃይማኖት ሳይለያቸው በአብሮነት መስዋዕትነት ከፍለው ነጻነቷ የተከበረች ሀገር ለአሁኑ ትውልድ ያስረከቡት በነበራቸው አንድነት መኾኑን አንስተዋል።
በዚህ የጋራ ሀገረ ግንባታ ሂደት ውስጥም በባሕል እና በቋንቋ የተጋመደ ማሕበረሰብ ተፈጠሯል ብለዋል።
አሁን ላይ በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ ችግር አብሮነታችንን የሚያዳክም መኾኑን ያነሱት አፈ ጉባኤዋ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ተቀራርቦ መፍታት ለዴሞክራሲያዊ ግንባታ፣ ለሕዝቦች ሰላም እና ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት መከበር አቅም ይፈጥራል ብለዋል።
በክልሉ የተፈጠሩ ችግሮች እንዲፈቱ ደግሞ በየደረጃው የሚገኙ ምክር ቤቶች እየሠሩ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
የቀደመ አብሮነትን ለማጎልበት እና አሁን ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ግብረ ገባዊ እሴቶችንና ሕግጋትን በመቅረፅ፣ በማሳወቅና በማስተላለፍ ማኅበራዊ ተቋማት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ለዚህ ደግሞ ቤተሰብ የመጀመሪያውን ኀላፊነት ወስዶ በልጆች ላይ የመቻቻል፣ የአብሮነት፣ የአንድነት፣ የመረዳዳት እና መሰል ግብረገባዊ እሴቶች ላይ ሊሠራ ይገባል ብለዋል።
ከዚህ ባለፈ የመንግሥትና የትምሕርት ተቋማት፣ ቤተ እምነቶች የአንድን ግለሰብ ማንነትና ባሕሪ የመቅረጽ አቅማቸው ከፍተኛ በመኾኑ ትኩረት አድርገው እንዲሠሩ ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
