
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ስለ አብሮነት አዘውትሮ መናገር የሚያስፈልገው ለህልውናችን መቀጠል ዋስትና ስለሚሰጠን ነው። ኢትዮጵያዊ አብሮነት ስንል ኅብረት ፈጥሮ ሀገራችንን ከማንኛውም ስጋት በመጠበቅና በማበልፀግ በሁሉም መስክ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እና በፈታኝ ወቅቶችም በጋራ በመቆም ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅማችንን ማረጋገጥ ነው።
አብሮነት ኅብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን የሚያፀና፣ ብዝኃነታችንን የጥንካሬያችን ምንጭ የሚያደርግ፣ አንዳችን ለሌላችን በማሰብ ከብረት የጠነከረ አንድ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የሚፈጥር እሳቤ እንዲሁም ተግባር ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በደም፣ በኢኮኖሚ፣ በታሪክ፣ በሀይማኖት፣ በሥነልቦና፣ በባህል፣ እና በሌሎችም ማኅበራዊ እሴቶች የተጋመደ የአንድ ታላቅ ሀገር ሕዝብ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ የትናንት ማንነቱ፣ የዛሬ ህልውናው እና የወደፊት ዕጣፈንታው የተሳሰረ በመሆኑ የባህላችን እሴት፣ የአይበገሬነታችን ምንጭ የሆነው አብሮነቱን አጥብቆ መቀጠል አማራጭ የሌለው መንገድ ነው። መከፋፈል እና መለያየት እንደ ሕዝብ እና ሀገር ከማሳነስ በስተቀር የሚያመጣልን ትርፍ እና ድል የለውም።
ኢትዮጵያዊያን በኅብር ሀገር ገንብተዋል፤ ሕዝቦቿን በአብሮነት ከማንኛውም ባዕድ ወራሪ ለመጠበቅ እና በራሳችን ነፃነት መወሰን እንደምንችል በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች አሳይተናል። ኢትዮጵያ በአንድነቷ ታፍራ እና ተከብራ እንድትቆይ አባቶቻችን መሥዋዕትነት ሲከፍሉ አብሮነት ለሀገር ህልውና ያለውን ዋጋ በመመዘን ነው።
አዲሱ ትውልድም በሀገሩ አንድነት እና በሕዝቦች አብሮነት ላይ በውስጥ ባንዳዎችም ሆነ በውጭ ጠላቶች የሚሰነዘሩ ማናቸውንም ጥቃትና እና የሚዘረጉ የሴራ ገመዶችን በመረዳት ልክ እንዳባቶቹ ለአብሮነት ቀናዒ መሆን አለበት። አንድነታችንን ለመድፈር እና አብሮነታችንን በፅንፈኝት አስተሳሰብ ሊሸረሽሩ የሚፈልጉ አካላትን ጆሮ በመንፈግ ልናወግዛቸው ይገባል።
አንድነታችንን በመናድ ሊያዳክሙን የሚፍጨረጨሩ ፅንፈኞችን ተባብረን ድብቅ የፖለቲካ ዓላማቸውን በማክሰም የሀገራችንን ደህነትና የሕዝቦቿን ሠላም ማረጋገጥ ከሁሉም ይጠበቃል። አብሮነት የማይጥማቸው ፅንፈኞች ብሔርን ከብሔርን፤ ሃይማቶትን ከሃይማኖት በማጋጨት የቆየ አብሮነታችንን ለመናድ ብዙ ርቀት ቢጓዙም መቼም ቢኾን እንደማይሳካለቸው ልናሳያቸው ይገባል።
ዛሬ የአብሮነት ቀንን ስናከብር ሀገራችን ኢትዮጵያ በኅብር የተገነባችና በጋራ መሥዋዕትነት ተጠብቃ የቆየች መሆኗን ወደ ኋላ መለስ ብለን ማሰብ ይኖርብናል። እጣፈንታችን በእጅጉ የተሳሰረ መሆኑን ይበልጥ በመገንዘብ አብሮነታችንን የሚፈታተኑ ተግባራትና አስተሳሰቦችን ለመታገል ቁርጠኝነታችንን የምናድስበት እለት መሆን ይኖርበታል።
መልካም የአብሮነት ቀን ይሁንልን!!
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!