“ኢትዮጵያ ተባብረን ከሠራን ተስፋ ያላት ሀገር ናት” ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ

95

ባሕር ዳር: ጳጉሜ 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) “ጳጉሜን ለኢትዮጵያ” ሀገራዊ ንቅናቄ የጳጉሜን አምስተኛ ቀን ላይ ደርሷል፡፡ ጳጉሜን አምስት የትውልድ ቀን “ኢትዮጵያ የትውልዶች ድምር” በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ነው፡፡ የትውልድ ቀን በአዲስ አበባ ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባት አርበኞች እና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት እየተከበረ ነው፡፡ በዝግጅቱ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ በዓለም የተፈጠሩት ፈጠራዎች፣ ጦርነቶች፣ የተከሰቱ ወረርሽኞች፣ የተካሄዱ የኢንዱስትሪና የፖለቲካ አብዮቶች፣ አዳዲስ ግኝቶች የአንዳንድ ትውልዶች ማስታወሻ የኾኑባቸው ሀገራት ጥቂት አለመኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ በሀገር ደረጃ ባበረከቱት አስተዋጽዖ በፈጠሩት ተጽዕኖ በክፉም በደጉም የሚታወሱ ትውልዶችን ዓለማችን አይታለች ነው ያሉት፡፡

ማንኛውም ነገር የተገነባው በትውልድ ቅብብሎሽ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ ማንኛውም ትውልድ ራሱን ሊጠይቅ የሚገባው መሠረታዊ ጥያቄ ለቀጣዩ ትውልድ ምንድን ነው የማስረክበው የሚለውን መኾን እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ ዛሬን ብቻ፣ የተወሰኑ ጉዳዮችን ብቻ፣ የተወሰኑ ሰዎችን ብቻ፣ ፍላጎትን ማሟላት ብቻ ሳይኾን ተተኪው ትውልድን ያገናዘበ መኾን አለበትም ብለዋል፡፡

የወጣትነት ዘመናቸውን ያስታወሱት ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ በወጣትነት ዘመኔ ወደ ሌሎች ዓለማት ስሄድ የዓለም እምብርት ናት የምንላት ሀገራችን ወደኋላ መቅረቷን የተረዳሁ ያኔ ነውም ሲሉ አስታውሰዋል፡፡ በወጣትነት ዘመናቸው የነበረው የተማሪዎች ማኅበር ብዙ ነገር እንዳስተማራቸው እና ይሕ ማኅበር በዚህ ዘመንም ሊኖር እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡

በትውልዶች መካከል ያለው ግንኙነት የተቆረጠ ሳይኾን የተያያዘ ሰንሰለት ነውም ብለዋል፡፡ እያንዳንዱ ትውልድ የራሱ ችግሮችም አመች ኹኔታዎችም አሉት ነው ያሉት፡፡ ጥፋትን እና ችግርን የቀድሞው ትውልድ ላይ መጣል፣ ያለፈን መውቀስ፣ የአሁኑ ወጣት ደግሞ ብዙም ሳይሠራ ማወደስ የሚለው ላይ በጥንቃቄና ሚዛናዊ በኾነ አካሄድ ስንሄድ ነው የትውልዶች ሽግግር በጥሩ ኹኔታ የሚቀጥለው ብለዋል፡፡

መወቃቀስ ብቻ ሳይኾን የመፍትሔ ሃሳብ ይዞ መምጣት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ በትውልዶች መካከል የዕውቀት የልምድ ልውውጥ የማይናቅ ቦታ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡ ትውልድን ሊያንጽ ከሚችለው አንዱ ጉዳይ ማንበብና መመራመር መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ወጣቱ ትውልድ ማንበብ ፣መመራመር እና የመሞገት መንፈስ እንዲኖረው እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡ ሁሉንም አሜን ብሎ ሳይኾን ዐውቆ እንዲቀበል ያደርገዋልም ነው ያሉት፡፡ ማንኛውም ተግባር በሕዝብ ሊተች እንደሚችልም ያሳየዋል ያሉት ፕሬዚዳንቷ በሕዝብ መተቸት የሕዝብ ተቃውሞ አይደለም ፤ መተቸት እንድንችል ጥሩ አስተሳሰብ መላበስ አለብን ብለዋል፡፡

ሰው ሊማር የሚችለው ባቆየው ነገር ላይ መኾኑንም ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ ተናግረዋል፡፡ እኛ የምናልፍ ነን ፤ የሚያስተምሩት በሰነድ የተቀረጹት ናቸውም ብለዋል፡፡ ታሪክን በቅጡ ዐውቀን እና መዝግበን ካልተራመድን ወደፊት የሚገጥመንን ለመቋቋም እንቸገራለን ነው ያሉት፡፡ በዓለም ላይ ሊገታ የማይችለው ለውጥ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ ኹኔታዎቹ እየተቀየሩ በሄዱ ቁጥር ለችግር መፍቻ መፍትሔ ማምጣት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ለውጥ መሠረቱ ጽኑ መኾን እንደሚገባውም ገልጸዋል፡፡

ለውጥ እንዲጸና ጽኑ እሴቶች እንደሚያስፈልጉ የተናገሩት ፕሬዚዳንቷ በአንድ ትውልድ እና በሌላ ትውልድ መካከል ሃቀኝነት፣ ታማኝነት፣ ሀገር ወዳድነትና ታታሪነት መኖር አለባቸውም ብለዋል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች የማይለወጡ መሠረታዊ ጉዳዮች ናቸው ፤ ይሄንን ትተን የትም አንደርስም ነው ያሉት፡፡ መጪው ትውልድ በርካታ ፈተናዎች ያሉበት መኾኑንም አንስተዋል፡፡

ከተረካቢው ትውልድ ላይ የምንተክለው እሴት ሊኖረን ይገባልም ብለዋል፡፡ ማኅበረሰቡ የሚያስተላልፈው እሴት ጥሩ ዜጋ እንድንኾን ያደርገናልም ነው ያሉት፡፡ የሀገር ፍቅርና ሀገርን ማገልገል ላይ መላላት እንደገጠመም ተናግረዋል፡፡ በአቋራጭ ሳይኾን በአግባቡ የታነጸና የተማረ ትውልድ እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት፡፡ ትምህርት መተኪያ የሌለው ጉዳይ መኾኑን ያነሱት ፕሬዚዳንቷ ጥራት ያለው ትምህርት ለትውልድ አስፈላጊ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ በትምህርት መፍትሔ ያለው ትውልድ መፍጠር እንደሚቻልም አመላክተዋል፡፡

ልዩነት በጦርነት የማይፈታ መኾኑን የሚያምን ፤ በሀገር ጉዳይ ላይ ቦታ እንዳለው የሚያውቅ ፤ መብቱን የሚጠቀም ፣ ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግር ትውልድ መፍጠር ይገባናልም ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ለውጦች ስርነቀልና አብዮት ኾነው ስብራትን እየፈጠሩ የሄዱ መኾናቸውን የተናገሩት ፕሬዚዳንቷ ከዚያ ማገገም ብዙ ጊዜ እየፈጀብን ፤ ትውልድ ላይ ተጽዕኖ እየፈጠረ ቆይቷል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ ተባብረን ከሠራን ተስፋ ያላት ሀገር ናት ፤ መነጋገርን፣ ሃሳብ መለዋወጥን፣ በሃሳብ መሞገትን ካስቀደምን ተስፋ ያላት ናት ብለዋል፡፡ አምላክ ያደላት እና ብዙ ያላት ሀገር መኾኗንም አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያን ብዙ ያላት ሀገር እያልን ድኃ የኾነች ሀገርን ለትውልድ ማስረከብና መንገር አስቸጋሪ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ተስፋ ቆርጨባት አላውቅም ፤ ተስፋ ያላት ሀገር ናት። እኛ ከተባበርን ፣ ችግሮቻችን በውይይት ለመፍታት ከሞከርን ፣ ቃታ ለመሳብ ካልቸኮልን ፣ ችግር በውጊያ ይፈታል ካላልን የምንደርስበት ወሰን የሌለው ነውም ብለዋል፡፡ ካለፈው ዓመት ተምረን የደስታና የደስታ ዘመን እንዲኾን እመኛለሁም ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleወጣቶች ጥንት አባቶቻቸው ያቆዩላቸውን አንድነት እንዲያጠናክሩ የኢትዮጵያ አረጋውያን ማኅበር አባቶች ጠየቁ፡፡
Next articleማኅበራዊ ተቋማት ግብረ ገባዊ እሴት ላይ አተኩረው እንዲሠሩ አፈጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ጥሪ አቀረቡ።