“በቀጣይነት እየገነባነው የምንሄደው ትውልድ ኢትዮጵያዊነቱን ከአፍሪካዊነቱ፣ አፍካዊነቱን ከዓለም አቀፋዊነቱ ያጣመረ ሊሆን ይገባል” የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

61

ባሕር ዳር: ጳጉሜን 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የትውልድ ቀንን በማስመልከት መልእክት አስተላልፏል።

ሙሉ መልእክቱ ቀጥሎ ቀርቧል፦
የትውልዶች ድምር ሀገር- ኢትዮጵያ!
የዛሬው ትውልድ የትናንት ትውልድ ወራሽ ነው፡፡ ነገ ደግሞ በዛሬው ትውልድ አሻራ ይገነባል፡፡ የትናንት በጎና መጥፎ ነገር ለዛሬ እንደተረፈው ኹሉ፤ የዛሬ ሥራም የነገን ዕጣፈንታ በእጅጉ ይወስናል፡፡ ይህ የማይቀየር እውነታ ነው፡፡ ኢትዮጵያም በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬ ላይ የደረሰች የትናንት ታሪካችን፣ የዛሬ ማንነታችን እና የነገም ተስፋችን ናት፡፡ የትናነት በጎ ታሪኳ ለዛሬ ወርቃማ እሴት ኾኖ እንደሚያገለግለው ኹሉ፤ መጥፎ ጠባሳ ጥለው ያለፉ የትናንት ክስተቶችም ለዛሬው ትውልድ የግጭት እና የኋላቀር አስተሳሰቦች ምንጭ ኾነው እንዳይቀጥሉ በአንክሮ መሰራት አለበት፡፡

የትናነት ክስተቶች በዛሬያችን ላይ ተፅዕኖ እንዳሳደሩ ከተገነዘብን፤ ከትናንት ምን ወርሰን ለነገ ምን አሻራ እናኑር? የሚለውንም በከፍተኛ ትኩረት ልናስብበት ይገባል፡፡ ከትናንት ስህተት ተምረን፣ መልካም እሴቶችን ደግሞ አጎልብተን መጠቀም ከቻልን ለነገው ትውልድ የበጎ እሴቶች በረከት እንደምናወርስ አያጠራጥርም፡፡ ትናንትን እና ነገን አስተሳስሮ መልካሙን የማጎልበት፤ መጥፎውን ደግሞ የማስቀረት አቅም ያለው የዛሬ ተግባራችን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያችን ከትናንት የወረሰቻቸው እጅግ ብዙ ጠቃሚ እሴቶች አሉ፡፡ ጀግንነት፣ የሀገር ፍቅር፣ አብሮነት፣ እንግዳ ተቀባይነት፣ መልካምነት፣ ደግነት፣ ዘርፈ ብዙ የእርስ በእርስ መስተጋብር ወዘተ… ልናዳብራቸው የሚገቡ በታሪካችን የወረስናቸው የእኛነታችን መገለጫ አኩሪ የትውልድ ሃብት ናቸው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በተለይም በፖለቲካው መስክ ልዩነቶችን በሰላማዊ ውይይት አለመፍታት፣ ያልዳበረ የዴሞክራሲ ባህል፣ አለመደማመጥ፣ አለመተማመን፣ አክራሪነት፣ ጠመንጃ ነካሽነት ወዘተ… ሀገራችን እጅግ ብዙ መስዋዕትነት እንድትከፍል አድርጓታል፡፡ በዛሬው ዕለት የትውልድ ቀንን ስናከብር “የወል ትርክቶችን መሠረት ያደረገ የመደመር ትውልድ እንዴት ይገንባ?” የሚለውን ጉዳይ በሚገባ ልንነጋገርበት ይገባል፡፡ የመደመር ትውልድ ሲባል ልዩነቱን የሚያከብር እና አንድነቱን የሚያጠናክር ማለት ነው፡፡ በግል እና በማኅበር ያለው ማንነቱ የማይጋጭበት፣ ልዩነትን የውበት እና የአቅም ምንጭ አድርጎ የሚጠቀም፣ እኩልነትን በመከባበር እና አብሮ በማሸነፍ ውስጥ የሚመለከት፣ ደስታውን በመጋራት የሚያበዛና ችግሩን በመካፈል የሚቀንስ፣ አብሮ በማሸነፍ የሚያምን የመደመር ትውልድ መፍጠር ይገባል፡፡

እንደ ማኅበረሰብ በቀጣይነት እየገነባነው የምንሄደው ትውልድ ኢትዮጵያዊነቱን ከአፍሪካዊነቱ፣ አፍካዊነቱን ከዓለም አቀፋዊነቱ ያጣመረ ሊሆን ይገባል። በመደመር እሳቤ የሚመራ ትውልድ ከትናንት የተቀበላትን ኢትዮጵያ የተደበቀ ውብ ማንነቷን ገልጦ፣ ስጦታዎቿን ጠብቆና አሻሽሎ ለቀጣዩ ትውልድ የሚያስተላልፍ እንዲኾን ሁላችንም የሚጠበቅብንን ድርሻ መወጣት ይገባናል፡፡

እንኳን ለጳጉሜን 5/2015 የትውልድ ቀን አደረሳችሁ!

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ምርታማነት የአንድን ሀገር ሕልውና፣ ተከብሮ የመኖርና ያለመኖርን እጣ ፋንታ የሚወስን ነው” ስቡህ ገበያው (ዶ.ር)
Next article“የሕዳሴው ግድብን አራተኛና የመጨረሻ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ሳበሥር በታላቅ ደስታ ነው።” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)