
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) “ጳጉሜን ለኢትዮጵያ” ሀገራዊ ንቅናቄ መካሄዱን ቀጥሏል፡፡ ጳጉሜን አራት የአምራችነት ቀን “ ከሸማችነት ወደ አምራችነት” በሚል መሪ ሃሳብ የአምራች ዘርፉን የሚያነቃቁ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡
የአማራ ክልል ሥራና ስልጠና ቢሮ ኀላፊ ስቡህ ገበያው (ዶ.ር) ቀኑን አስመልክተው መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ በመልእክታቸውም አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የመረጋጋት፣ የፍቅር፣ የደስታና የአንድነት ዓመት እንዲኾን ተመኝተዋል፡፡ የአምራችነት ቀን ለተቋማቸው ታላቅ እሳቤና ኀይል መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ በአዲሱ ዓመት ሰላምን በማጠናከር፣ የሥራ ባሕልና ወኔን በመላበስ ክልሉን ወደፊት ለማራመድ የምንሠራበት ጊዜ መኾን ይገባዋል ነው ያሉት፡፡
ምርታማነት የአንድን ሀገር ሕልውና፣ ተከብሮ የመኖርና ያለመኖርን እጣ ፋንታ የሚወስን ነው ብለዋል፡፡ ማምረት የተሳነው ማኅበረሰብ ሀገሩን ለበዓድ እሳቤዎች አሳልፎ እንደመስጠት እንደሚቆጠርም አመላክተዋል፡፡ አምራች ኀይል መፍጠር ለአንድ ሀገር ሕዝብ ልዕልና፣ ሰላም፣ ብልጽግና እና አንድነትን ለመፍጠር ዓይነተኛ ዘዴ ነው ብለዋል፡፡
በየትኛውም የአማራች ዘርፍ ከፍተኛ ጥራትና ብዛት ያለው ምርት ለማምረት በመጀመሪያ ደረጃ ጠንካራ የሥራ ባሕል ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ ሙያዊ ክህሎትና ስልጡን የሰው ኀይል ለአምራች ዘርፉ አስፈላጊዎች መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ አምራች ዘርፉ የሥራ እድል ለመፍጠር፣ ኢኮኖሚን ለማሳደግ እና ችሎታ ያላቸውን ግለሰቦች ለማበረታታት አስተዋጽዖው የላቀ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ የሰለጠነ የሰው ኀይል ለሀገር መሠረታዊ ለውጥ እንደሚያመጣም ገልጸዋል፡፡
ወጣቶች በኢንተርፕራይዝ በመደራጀት የሥራ እድል እንደተፈጠረላቸውም ገልጸዋል፡፡ በኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው እየሠሩ ያሉ ወጣቶች ከራሳቸው አልፈው ለሀገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያደረጉ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ዝቅተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለታላላቅ ኢንዱስትሪዎች መሠረት መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡
በተቋማቸው ሥር የሚሠሩ ሥራዎች ሕዝብን በማገልገል፣ የኑሮ ውድነትን በመግታት፣ ለገበያ አማራጭ ይዞ በመቅረብ ጥሩ ሥራዎች እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ወጣቶች በሥራ ፈጠራና በሥራ ክህሎት ተደራጅተው ከራሳቸው አልፈው ሀገር የሚጠቅም ሥራዎችን እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ ለመቀጠል ሰላም ወሳኝ ጉዳይ መኾኑን ያነሱት ኀላፊው ሰላም የሁሉም መነሻ ነው፣ ሰላማችን አስጠብቀን፣ ብቁ ዜጎችን በማፍራት የሥራ እድል መፍጠር ይገባል ነው ያሉት፡፡
ክልሉን ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ ሰላም ወሳኝ ጉዳይ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ በቀጣይም ዓመት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ለሚኾኑ የክልሉ ነዋሪዎች የሥራ እድል ለመፍጠር ማቀዳቸውን አስታውቀዋል፡፡ የታቀደው እንዲሳካ ሰላምን መጠበቅና በአንድነት መቆም ይገባልም ብለዋል፡፡ ሁሉም ዜጋ የሰላም ዘብ እንዲኾንም ጠይቀዋል፡፡ ሰላም ሲኖር እቅዶች ይሳካሉ፣ የተጀመሩ ሥራዎች ይፋጠናሉ፣ ክልሉን በሁሉም መስክ ከፍ ማድረግ ይቻላል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
