
አዲስ አበባ: ጳጉሜ 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በበጎ አድራጎት ሥራዎች ከደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት የተቀበሉት ክቡር ዶክተር ዓለማየሁ ስመኝ በሕይወት ዘመናቸው ላበረከቱት የልማትና በጎ አድራጎት ሥራዎች በአዲስ አበባ የደቡብ ጎንደር ተወላጆችና የደብረታቦር ከተማ በመተባበር ነው የዕውቅና ፕሮግራሙ የተዘጋጀላቸው ።
በዕውቅና መርሐ ግብሩ የዕለቱ ተመሥጋኝ ክቡር ዶክተር ዓለማየሁ ስመኝ ፣ የዕለቱ የክብር እንግዳ ክቡር አምባሳደር አያሌው ጎበዜ ፣ የደብረ ታቦር ከተማ ከንቲባ ደሳለኝ በላቸው ፣ የቀድሞው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ፕሮፌሰር መንገሻ አድማሱ፣ የሚድሮክ ኢንሸስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጀማል አህመድን ጨምሮ ቤተሰቦቻቸው ፣ ወዳጆቻቸው እና በርካታ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
ክቡር ዶክተር ዓለማየሁ ስመኝ ማናቸው? የሚለው በፕሮፌሰር መንገሻ አድማሱ ቀርቧል።
በታሪኩ እንደቀረበው ክቡር ዶክተር ዓለማየሁ ስመኝ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ተምሳሌት ሰዎች አንዱ ናቸው።
ታታሪ፣ ብርቱ፣ ሀገር ወዳድ መልካም ሥነ ምግባር ያላቸው እና ዘመን ተሻጋሪ የልማት ቀንዲል የበጎ ሥራ ተምሳሌት በመኾንም ይታወቃሉ፡፡
ግለሰቡ በንግድ ዘርፍ በርካታ ሥራዎችን ለሀገራቸው አበርክተዋል። በትምህርት ዘርፍም በርካታ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ይታወቃሉ። በመሰረተ ልማት ግንባታ እና በጤና ተቋማት ግንባታም ትልቅ አበርክቶ ያላቸው ባለሀብት መኾናቸው ተገልጿል።
በዕውቅና ሥነ ሥርዓቱ የተገኙት የዕለቱ የክብር እንግዳ አምባሳደር አያሌው ጎበዜ የዕለቱ ተመሥጋኝ በኢንሸስትመንትና በንግድ ዘርፍ ግንባር ቀደም ሚና የተጫወቱ ዕውነተኛ ባለሃብት ናቸው ሲሉ ያላቸውን ክብር ገልጸዋል።
ከረዥም ዓመታት በፊት ኢንደስትሪ መር ኢኮኖሚን እና ኤክስፖርት መር ኢንዱስትሪን ቀድመው የተረዱ ወደ ውጭም እሴት ጨምረው መላክ የጀመሩ የመጀመሪያው ቁርጠኛ አምራች ባለሃብት ናቸውም ነው ያሉት።
ግብርን በትክክልና በወቅቱም በመክፈል አርአያ ናቸው ያሉት አምባሳደሩ በትምህርት ፣ በጤና ፣ በበጎ አድራጎት፣ በቱሪዝምና በሌሎችም ዘርፎች ክቡር ዶክተር ዓለማየሁ ላበረከቱት አስተዋፅኦ ምሥጋና አቅርበዋል።
የደብረታቦር ከተማ ከንቲባ ደሳለኝ በላቸው ለክብርና ለታላቅነት ልክና መስፈሪያ ያለው ሰው ታላቅ ነው ፤ ክቡር ዶክተር ዓለማየሁ ይህንን ያሟሉ ናቸው ብለዋቸዋል።
እንደጉና ታላቅ የኾኑ ናቸው ይህንንም ያስባለኝ ሥራቸው ነው ያሉት ከንቲባው እንደዚህ በሕይወት እያሉ ማመሥገንና ማክበር መቻል ትልቅ እድል ነው ብለዋል ከንቲባው።
ላከበራችሁኝ ሁሉ በፈጣሪ ሥም አመሠግናለሁ ያሉት ክቡር ዶክተር ዓለማየሁ ስመኝ ዳረጎቴን አሻግሩ የሚለውን መልዕክቴን አደራ ብለዋል፡፡
መስጠት እንደማያጎድል አይቸዋለሁ ሀብት ማለት ለሌላው መስጠት ለሕዝብና ለሀገር ልማት ማዋል ነው ይህንን ዛሬ ላይ ኾኜ ወደኋላ ተመልክቼ ያረጋገጥኩት ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
በአንድነት እና በፍቅር አደራ ተረካቢ እንሁን ፣ እንሥራ ከድህነት እንውጣ ለሰላም እንሥራ ብለዋል ክቡር ዶክተር አለማየሁ ስመኝ ።
በዕውቅናውም ለተመሥጋኙ የተዘጋጀ ሙዚቃና ግጥም ምስክርነት ተሰጥቷል። የክብር ካባም በክብር እንግዳው አማካኝነት ተበርክቶላቸዋል።
ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግሥቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
