
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የኮሌራ ወረርሽን ለመከላክል ታላሚ ያደረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ የውይይት መድረክ ከባለድርሻ አካላት ጋር በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል፡፡
በሀገሪቱ ከተከሰተ ከአንድ ዓመት በላይ እንዳስቆጠረ የተነገረለት ኮሌራ በርካቶችን ለከፋ ሕመምና ሞት እንደዳረገ ነው በመድረኩ የተነሳው፡፡
ስለ ኮሌራ በሽታ ምንነት፣ ስርጭትና አደገኝነት፣ የመከላክልና ቁጥጥር ሥራ፣ ሕክምናው ላይ ለማኅበረሰቡ ሰፊ ግንዛቤ መስጠት እንደሚገባ ነው የተነገረው፡፡
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ እንደተናገሩት በሽታው እያደረሰ ካለውና ከሚያደርሰው የከፋ ጉዳት አንጻር ለመከላከልና ለመቀጣጠር በግንዛቤ ላይ የተመሰረተ ቅንጅታዊ አሠራር ያስፈልጋል፡፡
ዳይሬክተሩ በመድረ እንዳሉት ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በተደረገ ተከታታይ ጥናት ከዚህ ቀደም አጣዳፊ ትውከትና ተቅማጥ እየተባለ ይጠራ የነበረውን በሽታ አሁን ላይ ኮሌራ ብሎ በስሙ መጥራት ተገቢ ኾኖ ተገኝቷል ብለዋል፡፡
በክልሉ በተከሰተባቸው ዞኖች የመከላከልና ቁጥጥር ሥራ እየተከናወነ መኾኑን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ በቅንጅት በመስራት ስርጭቱን ዜሮ ማድረግ እንሚገባ አሳስበዋል፡፡
እናም የማሳወቅ፣ግንዛቤ መስጠትና ማንቃት ሥራው ላይ ሚዲያዎች፣የኮሚኒኬሽን ዘርፉ፣የሃይማኖት መሪዎችና ሌሎችም አካላት ተባብረው ከጤናው ዘርፍ ጋር ኮሌራን መከላከልና መቆጣጠር እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡
በሽታው በምእራብ ጎንደር፣ ማዕከላዊ ጎንደር፣ በሰሜን ጎጃም፣ በባሕር ዳር ዙሪያና በክልሉ ሌሎችም አካባቢዎች ቀደም ብሎ መከሰቱ ተገልጿል፡፡
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አብዱልከሪም መንግስቱ እንዳሉትም በሽታውን በሚገባ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለስርጭት እድል የሚፈጥሩና ተጋላጩን የኅብረተሰብ ክፍል በመለየት በትኩረት መሥራት ይገባል፡፡
ከቀጣይ መስከረም 5/2016 ዓ.ም ጀምሮ በተመረጡ ዞኖች የኮሌራ ክትባት ዘመቻ እንደሚካሄድ ተመላክቷል፡፡
ክትባቱ ማዕከላዊ ጎንደር፣ ሰሜን ጎጃም፣ ምዕራብ ጎንደር፣ ሰሜን ሽዋን ጨምሮ በክልሉ 8 ዞኖች ይሰጣል ነው የተባለው፡፡ ለዚህም ከቅድመ መከላከል እስከ ሕክምናው ድረስ ኅብረተሰቡ ተባባሪ መኾን አለበትም ተብለዋል፡፡
በመድረኩ ተሳታፊ የሃይማኖት መሪዎችም ለአሚኮ እንዳሉት ለኅብረተሰቡ ጤና ግንዛቤ በመፍጠር በኩል ኀላፊነታቸውን እንደሚወጡ ነው የተናገሩት፡፡
የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ መልዓከ ገነት አምደሃይመኖት ፈጠነ እንተናገሩት የጤና ባለሙያዎች በሚሰጡት ግንዛቤ መሰረት በሽታው ኅበረተሰቡን እንዳይጎዳ ፣የተሳሳቱ መረጃዎችን እያጠሩ በማረም በኩል ማኅበረሰብ ያማንቃት ኀላፊነታቸውን እንደሚወጡ ነው ያስረዱት፡፡
የጎንደር ከተማ እስልምና ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አህመዲን አብዱልቃድር በበኩላቸው ከክትባት ጋር እና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ የሚነሱ ብዥታዎችን የማጥራት፣ ኮሌራ ከንጽህና ችግር ጋር እንደመገናኘቱ መጠን ከግለሰብ እስከ አካባቢን ማጽዳት ማኅበረሰቡን የማስገንዘብ ሚናችንን እንወጣለን ብለዋል፡፡
እያንዳንዱ ሰው ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ፣ እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ሁሉ ለበሽታው ተጋላጭ ላለመኾን ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ተመላክቷል፡፡
ዘጋቢ፡-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!