“በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከ255 በላይ አዳዲስ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት ገበተዋል” የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ

35

ባሕር ዳር: ጳጉሜን 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ጳጉሜን 4 – የአመርችነት ቀንን ከአማራቾች ጋር አሳልፏል።

የአማራ ክልል ኢንዲስትሪ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ተፈሪ ታረቀኝ፣ የቢሮው የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች በባሕርዳር ከሚገኙ የአምራች ተቋማትን ተመልክተዋል።

የጨርቃጨርቅ ዘርፍ ላይ የተሰማራው የአለባቸው እና ማስተዋል ኅብረት ሥራ ሽርክና ማኅበር እና የዩኒሰን ዘይት ፋብሪካዎች ደግሞ ምልከታ የተደረገባቸ ተቋማት ናቸው።

የአለባቸው እና ማስተዋል ኅብረት ሥራ ሽርክና ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ይርጋ አይቸው የአማራችነትን ለማሳደግ እየሠራን ነው ብለዋል። ምርትና ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እየሠሩ መሆናቸውንም ገልፀዋል። ከሀገር ውስጥ ገበያ ባለፈ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል። ከውጭ የሚያመጧቸውን ጥሬ እቃዎች በሀገር ውስጥ ለመተካት እየሠሩ መሆናቸውንም ገልፀዋል።

ምርትና ምርታማነታቸውን ለማሳደግ በሚያደርጉት ሥራ የመብራት ኃይል መቆራረጥ እንቅፋት እንደሆነባቸውም ተናግረዋል። የማልሚያ ተጨማሪ ቦታ እንደሚያስፈልጋቸውም ገልፀዋል። አሁን ላይ 490 ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች እንዳሏቸውም ተናግረዋል።

የዩኒሰን ኮርፖሬት ጄኔራል ማናጀር አሻግሬ ጌትነት ፋብሪካቸው የአምራችነት ቀንን የበለጠ በመሥራት እያከበረው መሆኑን ገልፀዋል። ጥራት ያለው ምርትና አገልግሎት በማምረት ለደበኞች እያቀረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል። የዓመትበዓል ወቅትቸ በመሆኑ ያለው ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን የገለፁት ሥራ አስኪያጁ ፍላጎቱን ታሳቢ በማድረግ ያለ እረፍት እየሠሩ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

በቀን ከ33 ሺህ ሊትር በላይ ዘይት እንደሚያመርቱም ተናግረዋል። ምርትና ምርታማነታቸውን ለመጨመር ተጨማሪ የኢንቨስትመንት ቦታ እንደሚፈልጉም ገልፀዋል። ሃብትና ፍላጎት አለን ተጨማሪ የመሥሪያ ቦታ ግን እንፈልጋለን ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ተፈሪ ታረቀኝ፤ አማራችነት ከአማራ ሕዝብ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው፣ የአማራ ሕዝብ በአማርችነቱ የሚታወቅ ነው ብለዋል። አማራችነትን በተገቢው መንገድ እያዳበርን ባለመሄዳችን የአማራች ዘርፉ በሚፈለገው ልክ ሳያድግ ቆይቷልም ነው ያሉት። የአማራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ላይ ትኩረት አድርገው እየሠሩ መሆናቸውንም ገልፀዋል።

በአማራችነት ቀን በኢንዱስትሪ ዘርፉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረጉ ያሉትን የምናመሰግንበት፣ የኢንቨስትመንት ቦታ ወስደው ልማትን እያቀጨጩ ያሉ ባለሀብቶችን የምንወቅስበት ፣ በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ከአምራቾች ጋር እየተነጋገርን የምናሳልፍበት ነውም ብለዋል። የኢንዱስትሪ ዘርፉን ችግሮች ለመሻገር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርበርብ ማድረግ አለባቸው ነው ያሉት። በአማራ ክልል በዘርፉ የነበሩ አሰራሮችን በማስተካከልና የክልሉን ፀጋ ለይቶ በማውጣት ወደ ክልሉ የሚመጡ ባለሀብቶች ቁጥር መጨመሩን ገልፀዋል።

በክልሉ የተሻለ የአምራች ኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ መታየቱንም አስታውቀዋል። በሁለት እና ሦስት ዓመታት ውስጥ ለዓመታት ያልታዩ ታላላቅ ኢንዱስትሪዎች በክልሉ ወደ ግንባታና ምርት መግባታቸውንም ገልፀዋል። የኢንዱስትሪ ግንባታዎች እየተፋጠኑ መሆናቸውንም ተናግረዋል። መኪና መገጣጠሚያዎች፣ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፋብሪካዎች እና ሌሎች ታላላቅ ፕሮጀክቶች በክልሉ ሥራ መጀመራቸውንም ገልፀዋል። ክልሉ ካለው እድልና ፍላጎት አኳያ አሁንም በርካታ ሥራ እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል። አሠራርን ማስተካለል እና በዘርፉ ያሉ ችግሮችን መፍታት ለአምራች ኢንዱስትሪው እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለውም ገልፀዋል።

በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በርካታ ሥራዎችን እየሠሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል። በክልሉ በ2015 ዓ.ም ከ255 በላይ አዳዲስ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት መግባታቸውንም አስታውቀዋል። የክልሉን ሰላም ጠብቆና ያሉ ክፍተቶችን ሞልቶ መሥራት ከተቻለ ዘርፉ ታላቅ ተስፋ ያለው መሆኑን ገልፀዋል። በተለይም ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ያሉ ቸግሮችን ለመፍታት ከፌደራል መንግሥት ጋር እየሠሩ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

በማንፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ በበጀት ዓመቱ፦

👉 ከ62 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ተፈጥሯል

👉ከ138 ሚሊዮን ዶላር በላይ ከውጭ ምንዛሬ ገቢ ተገኝቷል።

👉ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማዳን ተችሏልም ብለዋል።

በአማራ ክልል ከ3 ሺህ 600 በላይ ዝቅተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውንም ገልፀዋል። የኢንዱስትሪዎችን አቅም ለማሳደግና አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን ለመሳብ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ምልከታ በተካሄደባቸው ተቋማት እየሠሩ ያገኘናቸው ሠራተኞችም አምራች ኢንዱሰትሪዎች ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደላቸው ገልፀዋል።

ኢትዮጵያን ከሸማችነት ለማውጣት ሁሉም አምራችነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባውም አመላክተዋል። ቀኑንም ታሳቢ በማድረግ ከወትሮው በተለየ እየሠሩ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየምርት ብክነት እንዳያጋጥም የድሕረ ምርት አያያዝ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንደሚገባ ግብርና ቢሮ አሳሰበ፡፡
Next articleከመጭው መስከረም ጀምሮ የኮሌራ በሽታ ክትባት በዘመቻ ሊሰጥ መኾኑን የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንቲትዩት አስታወቀ።