
ባሕር ዳር: ጳጉሜ 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጳጉሜን 4/2015 ዓ.ም የአምራችነት ቀን እየተከበረ ይገኛል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ቀኑን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ዘላቂ እድገት ለማምጣት፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የተረጋጋ ሰላም ለማስፈን የሀገሪቱ ዋነኛ የጀርባ አጥንት የኾነውን የግብርና ዘርፍ ማዘመን ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በምግብ ራስን ለመቻልና የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር የግብርና ግብዓትና ቴክኖሎጂ በስፋት በመጠቀም ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል ነው ያሉት ኀላፊው፡፡
በኢንዱስትሪ የበለጸጉ ሀገራት መነሻቸው ግብርና እንደኾነ ያነሱት ኀላፊው በኢትዮጵያም ግብርናውን በማዘመን ምርታማነትን ለማሳደግ ባለፉት ዓመታት ትኩረት ተሠጥቶ ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልልም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ እና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ሰብሎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መኾን ነው ያስገነዘቡት፡፡
ለዚህ ደግሞ የአኩሪ አተር እና የስንዴ ልማትን ለአብነት አንስተዋል፡፡
የሜካናይዜሽን እርሻን ለማስፋፋትም በክልሉ የእርሻ ትራክተሮችንና የእህል መሰብሰቢያ መሳሪያዎችን ለአርሶ አደሮች መሰራጨቱን አንስተዋል፡፡
የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት እና ምረጥ ዘር የማባዛት ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ አርሶ አደሩ ከአካባቢ ዘር ወጥቶ የተሻሻለ ዘር እንዲጠቀም የምርምር ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ለአርሶ አደሩ ዘመናዊ የግብርና አመራረትና አሥተራረስ ላይ ግንዛቤ እንዲኖረው የኤክስቴንሽን ስርጸት ሥራ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል፡፡
በማምረት ሂደት ውስጥ የምርት ብክነት እንዳያጋጥም አርሶ አደሩ የድህረ ምርት አያያዝ ሥራ ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሠራ አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!