
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አንተ ከዔደን ገነት የወጣህ፣ ገነትንም ታጠጣ ዘንድ የተመረጥህ፣ ከአፍላጋት ሁሉ የከበርክ፣ ከረዘሙትም የረዘምክ፣ አበው አደራ የሚጥሉብህ፣ አደራህንም ሳታስተጓጉል የምትመልስ፣ በቃል ኪዳኗ ምድር የፈለቅክ፣ ሕዝብ ሁሉ ባየህ ጊዜ የሚደስትብህ፣ ፍቅርና ደስታ የሚገበይብህ፣ እውቀትና ጥበብ የሚፈስስብህ፣ አንድነትና ታላቅነት የሚቀዳብህ፣ የደረቀው የሚለመልምብህ ግዮን ኾይ ምስጢርህ ምንድን ነው?
በሀሩር ውስጥ የሚኖሩትን የምታጠጣቸው፣ በበረሃ የሚሰቃዩትን ልምላሜን የምታጎናጽፋቸው፣ በደረቀ መሬት የሚኖሩትን የምትደርስላቸው፣ ከወንዝ ማዶና ማዶ ያሉትን በአንድነት የምታስተሳስራቸው፣ በፍቅር የምታንሳፍፋቸው፣ በደስታ የምታስዋኛቸው፣ ጥበብ የሚገኝብህ፣ ዓለማት ሁሉ ያዩህ ዘንድ የሚጓጉልህ፣ መነሻህን ያውቁ ዘንድ የሚጓዙልህ፣ ውበትህ እና ታላቅነትህን ያዩ ዘንድ በዙሪያህ የሚከትሙብህ ታላቁ ግዮን ኾይ የመወደድህ ምስጢር ምን ይኾን?
እረኞች ለዘመናት በዋሽንታቸው አጀቡህ፣ ዓለም አጫዋቾች ተቀኙልህ፣ አዜሙልህ፣ ፍቅራቸውን እና የመውደዳቸውን ልክ ገለጹልህ፡፡ ብዙዎች የተቀደስህ ወንዝ ነህና ቅዱሱ ወንዝ አሉህ፣ ለቅድስናህ የተገባውንም አደረጉልህ፣ ፍቅራቸውን እና አክብሮታቸውን ይገልጹ ዘንድም መስዋዕት አቀረቡልህ፡፡ በላይህ ላይ ቅዱስ መንፈስ አለ ሲሉም ተጠመቁብህ፣ ፈውስንም አገኙብህ፤ ግዮን ኾይ ከወንዝነት የተሻገረው ኃያልነትህ፣ ከውኃነት ያለፈው ምስጢርህ ምን ይኾን?
ዘመናት አልፈው ዘመናት በተተኩ ቁጥር በግዮን (በዓባይ) ወንዝ ዳር ሰዎች ይሰበሰባሉ፣ የተጠሙት ከወንዙ ውኃ ይጠጣሉ፣ ጠጥተውም ይረካሉ፡፡ ግዮንን እንኳን ዋሽንት ይዘው የሚወርዱ እረኞች፣ እንኳን ዜማና ቅኔ ከአንደበታቸው የሚያወጡ ባለቅኔዎች፣ እንኳን ምስጢር የሚያሜሰጥሩበት፣ ተመስጦን የሚያገኙበት፣ አደራ የሚጥሉበት አባቶች፣ እንኳን ውኃ በእንሥራ የሚቀዱበት፣ የለመለመ ቄጤማ የሚቀጥፉበት እናቶች፣ እንስሳትም ይናፍቁታል፡፡ ከጥማቸው ይረኩበታል፣ ደስታና ሀሴትን ያገኙበታል እና ይጓጉለታል፣ አብዝተውም ይናፍቁታል፡፡
አበው ምስጢር ያሜሰጥሩበታል፣ ጥበብ ይቀዱበታል፣ እውቀት ይጨልፉበታል፤ ታሪክ ይጽፉበታል፣ የመወደድን እና የመከበርን ነገር ያዩበታል፡፡ ታላቁ ወንዝ ሕዝብን ከሕዝብ ሲያፋቅር የኖረ፣ በፍቅር ያስተሳሰረ፣ በደስታ ያከበረ ነው፡፡ ከወንዝ ማዶ እና ማዶ ኾነው የሚኖሩ በግዮን ወንዝ በአንድ ላይ ይገናኛሉ፡፡ ከአንድ ወንዝ ይጠጣሉ፣ ከአንድ ወንዝ ይዋኛሉ፣ ከአንድ ወንዝ ፍቅርን ይቀዳሉ፣ ከአንድ ወንዝ ደስታን ይገበያሉ፣ ሰላምና አንድነትን ይጨልፋሉ፡፡ በአንድ ወንዝ ዳር ማዕድ ቆርሰው፣ በአንድ መሰቦብ ይመገባሉ፣ ከእንሥራው ጠጅና ጠላ አዝንብለው በአንድነት ይጠጣሉ፣ በፍቅርም ይጋመዳሉ፡፡ ግዮን (ዓባይ) ልዩ መገናኛቸው፣ መተሳሰሪያ ገመዳቸው፣ መገናኛ ሥፍራቸው ነው፡፡ እነኾ አሮጌው ዓመት ዳግም ላይመለስ ሊሰናበት ነው፡፡ አሮጌውን ዓመት ልታሰናብተው፣ አዲሱን ዓመትም ልታበስረው ወረኃ ጳጉሜን ገብታለች፡፡ ወረኃ ጳጉሜን በኢትዮጵያ ብቻ ያለች፣ ለኢትዮጵያ ብቻ አሥራ ሦስተኛ ወር ኾና የታደለች፣ ለአሮጌውና ለአዲሱ ዓመት መሸጋገሪያ የኾነች፣ አልፍ አዕላፍ ምስጢራትን የያዘች ወር ናት፡፡ ይህች ወር በገባች ቁጥር የኢትዮጵያ ሊቃውንት ይወደሱበታል፣ ይታሰቡባታል፣ የሊቅነታቸው ጥግ ይመረመርባታል፣ ስማቸው እየተነሳ ይመሰገኑባታል፡፡ ለምን ካሉ ምስጢር አሜስጥረው፣ የረቀቀውን ተመራምረው፣ በምስጢር አጅበው የለዩዋት፣ ራሷን የቻለች ወር ያደረጓት እነርሱ ናቸውና፡፡
በወረኃ ጳጉሜንም በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር እጹብ የሚያሰኙ ነገሮች ይከወናሉ፡፡ ወንዞች ባዘቶ ይመስላሉ፣ ተራራና ሸንተረሮች በአደይ አበባ ይደምቃሉ፡፡ እረኞች ለአደይ አበባ ያዜማሉ፣ ጠብቆ ላደረሳቸው፣ ጠብቆም ለሚያቆያቸው አምላካቸው ይቀኛሉ፣ ምሥጋናም ያቀርባሉ፡፡ ወረኃ ጳጉሜን በገባች ጊዜ ልጆች ወፎች ሳይንጫጩ፣ ባዘቶ ወደ መሰለው ወንዝ ይወርዳሉ፣ እንኳን አደረስከን፣ ከርሞም ድገመን እያሉ ይጠመቃሉ፡፡ ቀናቱንም በዚሁ በደስታና በፍቅር ስሜት ያሳልፋሉ፡፡
ከቀናቱ ሁሉ ግን ጳጉሜን ሦስት የተለየች ትዝታ አላት፡፡ በዚህች ቀን የቅዱስ ሩፋኤል ዓመታዊ በዓል ይከበራልና፡፡ ልጆች በዚህች ቀን ዝናብ እንዲመጣ በጉጉት ይጠብቃሉ፡፡ ደመናው በሰማይ ሲጎተት“ ዝናቡ ቸሬ፣ አዝንበው ዛሬ” እያሉ በኅብረት ያዜማሉ፡፡ ዝናብ በመጣ ጊዜም ልብሳቸውን አውልቀው ዝናብ ይመታሉ፡፡ በዚች ቀን የምትዘንብ ዝናብ እንደ ሩፋኤል ጸበል ትቆጠራለች፡፡ ሩፋኤል ፈዋሽ የአምላክ ባለሟል መላክ እንደኾነ ይታመናልና፡፡ “ሩፋኤል አሳድገኝ፣ ሩፋኤል ከሽንብራው ጎተራ ክተተኝ” እያሉ ይጠመቃሉ፡፡ በዚህች ቀን ዝናብ ያልተመታና ያልተጠመቀ ልጅ በዓመት ብቻ የሚመጣ አንድ ታላቅ ነገር እንዳለፈው ያውቃልና ይከፋል፡፡ መከፋት እንዳይመጣም ቀኗን ጠብቆ በዝናብ ይጠመቃል፡፡
በወረኃ ጳጉሜን፣ በሦስተኛዋ ቀን፣ የበዓለ ሩፋኤል ዕለት ብዙዎች በደስታ ሲጠመቁ ይውላሉ፡፡ በዝናም ይመታሉ፡፡ ወደ ወንዝ ዳርም እየወረዱ ይጠመቃሉ፡፡ በዚህች ቀን በግዮን ( በዓባይ) ወንዝ ሠማይ ሥር ታላቅ ነገር ይደረጋል፡፡ ሕዝብ ሁሉ ከየአቅጣጫው ይሰባሰባል፡፡ ዓባይ አንደኛውን የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገር ከሌላኛው ክፍለ ሀገር ሕዝብ ጋር ሲያገናኝ የኖረ፣ እያገናኘም ያለ የአንድነት ገመድ፣ የአብሮነት ቤት ነው፡፡ በወረኃ ጳጉሜን በሦስተኛው ቀን ከደጀን እና ከጎሃ ጽዮን መካከል ከዓባይ ወንዝ ዳር ከአማራና ከኦሮሚያ ክልሎች የሚገኙ ብዙ ኢትዮጵያውያን ይገኛሉ፡፡ በተገናኙም ጊዜ በፍቅርና በደስታ ይሳሳማሉ፣ ዓመቱ እንዴት እንዳለፈ ይጠያየቃሉ፣ ለአዲሱ ዓመት ዋዜማ፣ ለታላቁ በዓልም እንኳን አደረሳች ይባባላሉ፡፡ አንደኛው ለአንደኛው የያዘውን የዘመድ መጠየቂያ ስጦታ ይቀባበላሉ፡፡ ፍቅርና ሀሴትንም ያደርጋሉ፡፡
በዚህች ቀን መነኮሳት፣ ቀሳውስትና ዲያቆናት ከማዶና ከማዶ ካሉ የበረሃ ውስጥ አብያተ ክርስቲያናት በልብሰ ተክህኖ ተውበው፣ በከበረ መጎናጸፊያ አክብረው ታቦታትን ያወጣሉ፡፡ በዚያ ሥፍራ የተሰበሰቡት ሁሉ ታቦታቱን በእልልታና በሆታ ያጅባሉ፡፡ ታቦታቱም ሕዝቡንና ምድሩን ይባርካሉ፡፡ በዓለ ሩፋኤልን ለማክበር የመጡ በአንድ ላይ በደስታ ይንሳፈፋሉ፡፡ በአንድነትም ወደ ዓባይ ወንዝ እየጠለቁ ይጠመቃሉ፡፡ በዚያች ምድር በበዓለ ሩፋኤል አንድነት፣ ፍቅር፣ ደስታና ኢትዮጵያዊነት ከፍ ብለው ይታያሉ፡፡ በዚያች ሥፍራ የተሰባሰቡ ሁሉ በአንደበታቸው ሳይነጋገሩ በልባቸው ይግባባሉ፡፡ ከአንደበታቸው ቃል ሳትወጣ በውስጣቸው ይግባባሉ፣ በፍቅር ይግባባሉ፣ በመልካም ልብ ይተዋወቃሉ፡፡
“በግዮን ሰማይ ሥር እንደዚህ ይኾናል
ደስታ እየተደራ ፍቅር ይሸመናል”
በግዮን ሠማይ ሥር ደስታ ይደራል፣ ፍቅር ይሸመናል፡፡ የተሸመነው ፍቅርም አያልቅም፣ አይቀደድም፣ በጋራ እንደለበሱት በጋራ እንዳጌጡበት፣ በጋራ እንዳማሩበት ይኖራሉ እንጂ፡፡ በጳጉሜን ሦስት በበዓለ ሩፋኤል ቀን ከአማራና ከኦሮሚያ ክልሎች ከዚያም አልፈው ከሌላ የኢትዮጵያ አካባቢ የሚመጡ ሁሉ በአንድነት እና በደስታ ያሳልፋሉ፡፡ በዓባይ ውኃ መጠመቅ ከድውይ ይፈውሳል ተብሎ ይታመንበታልና፣ የእምነታቸው እና የልባቸው መሻት ይፈጸም ዘንድ በጋራ ይጠመቃሉ፡፡ በአሮጌው ዘመን የነበረው አስከፊ ነገር ሁሉ ይወገድ ዘንድ በጋራ ይጠመቃሉ፣ በፍቅር ይውላሉ፣ በፍቅርም ይዋኛሉ፤ ልብ ለልብም ይገናኛሉ፡፡ ቀኑ ከባዱን ክረምት አሳልፈው፣ በሥራና በውኃ ሙላት ምክንያት ተራርቀው የቆዩት የሚገናኙበት ነውና ትልቅ ትርጉም ይሰጡታል፡፡
በሬዎች፣ በጎችና ፍየሎች ይታረዳሉ በዚያ የተሰባሰቡት ሁሉ በአንድ መሶብ፣ በአንድነት ይበላሉ፤ በአንድነትም ይጠጣሉ፡፡ ብዙዎች ለግዮን (ዓባይ) ከሚሰጡት ክብርና ግምት የተነሳ ዓመት ጠብቀው የእጅ መንሻ እየያዙ ይመጣሉ፡፡ ስጦታቸውንም በተመረጠው ቦታ ይሰጣሉ፡፡ ይህ ሥርዓት ከጥንት ዘመን ጀምሮ የነበረና ዛሬም ድረስ ያለ ኢትዮጵያውያን በፍቅር የሚያከብሩት ነው፡፡ በጋራ ተጠምቀው፣ በጋራ በልተው፣ ስለ አከራረማቸው ተጠያይቀው፣ ስለ አዲሱ ዓመት መልካም ምኞት ተለዋውጠው፣ አምላክ አክርሞ ያገኛቸው ዘንድ ተመኝተው፣ አደራውንም ሰጥተው፣ በፍቅር እየተሳሳሙ፣ በናፍቆት እየተላቀሱ ወደየመጡበት ይመለሳሉ፡፡ ዓመቱ ደርሶ እስከሚገናኙ ድረስም ይነፋፈቃሉ፡፡ ያችን የፍቅርና የደስታ ቀንም በጉጉት ይጠብቃሉ፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!