“በጎነት እንደ ሀገር መተሳሰብ፣ መረዳዳትና ማኅበራዊ ፍትሕ እንዲሰፍን ሚናው የላቀ ነው” ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይ

75

ባሕር ዳር: ጳጉሜን 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ የበጎነት ቀንን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ በሀገር አቀፍም ኾነ በዓለም ደረጃ የሴቶች የበጎነት አሻራ አርዓያነቱ ለትውልድ የተረፈ ተግባር ነው ብለዋል፡፡ በበጎነት ሥራ ሴቶችን ማሳተፍ ለሀገር ግንባታው መሰረታዊ ውጤት የሚያመጣ ተግባር ስለመኾኑም አንስተዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ እነ ማዘር ቲሬዛን፣ ከሀገር ውስጥም እነ ዶክተር አበበች ጉበናን የጠቀሱት ኀላፊዋ የበጎነት ተግባራቸው ትውልድ ሁሉ የሚኮራበት፣ የሰው ልጅ የበጎነት ጥግ የታየበት ተግባር ስለመፈጸማቸው ገልጸዋል፡፡ እናም የበጎነትን ቀን ስናስብ የእነሱን አርዓያነት እየወሰድን በተግባርም ዓመቱንም ሙሉ የበጎነት አበርክቷችን እያሳረፍን መኾን አለበት ብለዋል፡፡

“በጎነት እንደ ሀገር መተሳሰብ፣ መረዳዳትና ማኅበራዊ ፍትሕ እንዲሰፍን ሚናው የላቀ ነው” ያሉት ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይ ድጋፍ የሚሹትን፣ ችግረኞችን ከማገዘም ባሻገር ለሀገር ግንባታ ሚናው ከፍተኛ መኾኑ መታሰብ አለበት ብለዋል፡፡ ቢሮው በየዘርፉ የበጎ አድራጎት ሥራ ላይ ከተሰማሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየሠራ እንደኾነም ነው የተናገሩት፡፡ ዛሬ የበጎነት ቀንን አስመልክቶ የበጎነት ተግባርን ከቢሮው ጋር በቅንጅት በመሥራት ድጋፍ ለሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች አለኝታ ኾናችኋል በማለት ለተወሰኑ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የምሥጋና የምስክር ወረቀት አበርክተዋል፡፡

በጎነት የዘወትር ተግባር ነው ያሉት ኀላፊዋ ዛሬ ቀኑን የምናስበው በተግባር ነው ብለዋል፡፡ እናም ቢሮው ቀኑን አስመልክቶ ድጋፍ ለሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች የአዲስ ዓመት የበዓል መዋያ ድጋፍ አበርክቷል፡፡ ቢሮ ኀላፊዋ እንዳሉት ለበዓል መዋያ ድጋፍ የተደረገው ለ50 ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚኖሩ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ነው፡፡ ለእያንዳንዳቸውም አምስት ሺህ ብር የሚገመት ወጭ የተደረገበት የበዓል ዶሮ፣እንቁላል፣5 ሊትር ዘይት፣ሽንኩርት፣ፊኖ ዱቄትና እንዲሁም የብርድ ልብስ ድጋፍ ነው የተበረከተላቸው፡፡

አስተያየታቸውን የሰጡ የድጋፉ ተጠቃሚዎችም ስለተደረገላቸው ሁሉ አመሥግነዋል፡፡ መደጋገፍ ፣መተጋገዝና መተሳሰብ የሚኖረው ሀገር ሰላም ሲኾን ነው የሚሉት አስተያየት ሰጭዎቹ በሀገር ሰላም እንዲሰፍንም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

ቢሮው ቤተሰቦቻቸው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚኖሩ ለ55 ተማሪዎችም የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡

ዘጋቢ፡- ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article”የአማራ ሕዝብ ሰላም ወዳድነቱን በተግባር አሳይቷል” አቶ ይርጋ ሲሳይ
Next article“በግዮን ሰማይ ሥር እንደዚህ ይኾናል ደስታ እየተደራ ፍቅር ይሸመናል”