“እንግዶች ልክ ወደ ቤታቸው እንደመጡ እንዲሰማቸው የሚያደርግ ቅድመ ዝግጅት አጠናቅቀናል፡፡” የጎንደር ከተማ አሥተዳድር

172

ባሕር ዳር ጥር 8/2012ዓ.ም (አብመድ) እንግዶች በዓሉን በሰላምና በምቾት እንዲያሳልፉ ለማድረግ መዘጋጀቱን የጎንደር ከተማ አሥተዳድር አስታውቋል፡፡

የጥምቀት በዓልን ለመታደም ከ2 ሚሊዮን በላይ ጎብኝዎች ጎንደር ከተማን መዳረሻቸው ሊያደርጉ እንደሚችሉ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ማሳወቁ ይታወሳል። የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ መሪዎች፣ የጋሞ አባቶችና ወጣቶች፣ የሠላም ተጓዦች እንዲሁም የኤርትራ ልዑክ በበዓሉ እንደሚታደሙ ደግሞ የጎንደር ከተማ አስተዳድር ዛሬ ጥር 8/2012 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።

ከ15 ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች በበዓሉ ይታደማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ከተማ አስተዳደሩ ገልጿል። የጎንደር ከተማ አስተዳድር የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቻላቸው ዳኘው እና የከተማ አስተዳደሩ ሠላምና የሕዝብ ደኅንነት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተስፋ መኮንን በሰጡት መግለጫ “እንግዶች ልክ ወደ ቤታቸው እንደመጡ እንዲሰማቸው የሚያደርግ ቅድመ ዝግጅት አጠናቅቀናል” ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ሠላምና የሕዝብ ደኅንነት መምሪያ ኃላፊ እንደተናገሩት ሠላማዊ እንቅስቃሴ እንዲኖር የጸጥታ ኃይሉ ከአካባቢው ወጣቶች ጋር በጋራ እየሠራ ነው። ለሰላማዊ እንቅስቃሴው ከጎንደር ከተማ ባለፈ ለማዕከላዊ ጎንደር አጎራባች ከሆኑ ዞኖች ጋር በጋራ እየሠሩ እንደሚገኙም ገልጸዋል። በርካታ እንግዶች ወደ ከተማዋ ቀድመው መግባታቸውንና በቀሪ ቀናት የሚመጡ እንግዶች የሠላም ስጋት ሊገባቸው እንደማይገባም ነው ያረጋገጡት፡፡

እንግዶች በሚያርፉባቸው አካባቢዎች የተሻለ የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሟላት ከተማ አስተዳደሩ ከከተማዋ ባለሀብቶችና ከሚመለከታቸው አጋር አካላት ጋር በቂ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉንም በመግለጫቸው አመላክተዋል፡፡ የምግብም ይሁን የአልጋ ዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ የከተማዋ ነዋሪዎች ላይ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝና ይህን በማድረግ የከተማዋን ገጽታ የሚያበላሹ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

ወደ ከተማዋ የሚገቡ ጎብኝዎች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ የኢንተርኔትና የእጅ ስልክ ኔትወርክ መቆራረጥ ችግር እንዳይኖር፣ ከአሁን በፊት ለነበረው የከተማዋ የቴሌኮም አገልግሎት ችግርም ጊዜአዊ መፍትሄ ለመስጠት ኢትዮ ቴሌኮም በጥምቀተ ባህሩና በሌሎች አካባቢዎች ተንቀሳቃሽ ጣቢያዎችን ሲሠራ አብመድ ታዝቧል፡፡

ዘጋቢ:- ኃይሉ ማሞ

Previous articleርዕሰ መሥተዳድሩ እና ልዑካቸው ሞጣ ከተማ ላይ ጉዳት የደረሰባቸውን መስጊዶች እየጎበኙ ነው።
Next articleየፈተና ጥሪ ማስታወቂያ