”የአማራ ሕዝብ ሰላም ወዳድነቱን በተግባር አሳይቷል” አቶ ይርጋ ሲሳይ

70

ባሕር ዳር: ጳጉሜን 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ በክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫቸውም በክልሉ አንጻራዊ ሰላም መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ ሰላሙ ከቀን ወደ ቀን እየተሻሻለ፣ ሰዎች ሰላማቸውን እያገኙ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ በክልሉ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እየተሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡

አቶ ይርጋ በውጭም በውስጥም ያሉ ተጽዕኖዎች የክልሉን የልማት፣ የሰላም እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን እንደሚያባብሱም ተናግረዋል፡፡ በአንድ ሀገር ውስጥ አንድ ሕግ የሚያስከበር ኀይል እንጂ ሌላ ተገዳዳሪ ኀይል እንደማይኖርም ገልጸዋል፡፡ በአንድ ሀገር አንድ ሕግ አስከባሪ ኀይል ብቻ መኖር በኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን በሌሎች ሀገራትም የሚተገበር መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡

በክልሉ የነበረውን ቀውስ ለማብረድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁንም አስታውሰዋል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ ወዲህ ክልሉ መረጋጋቱን ነው የገለጹት፡፡ ከቁጥጥር ውጭ እየወጡ የነበሩ አካሄዶችም እየተሻሻሉና አንጻራዊ ሰላም እየተፈጠረ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ ሁሉም መጨነቅ ያለበት ለሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት መጠበቅ ሊኾን እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ በአጭር ጊዜ የመጣው ለውጥ ከፍ ያለ እንደኾነም አመላክተዋል፡፡

የክልሉ ነዋሪዎች በአንጻራዊነት እፎይ ብለው የሚሠሩበት አንጻራዊ ሰላም እየተፈጠረ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ሕዝቡ ለሰላም ባሳየው ቁርጠኝነት ክልሉ በአጭር ጊዜ ወደ ሰላም እየተመለሰ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ኢትዮጵያ ችግር ሲገጥማት አንድ ኾኖ ከችግር እንድትወጣ የሚያደርግ መኾኑን ያነሱት ኀላፊው አሁንም ሰላም ወዳድነቱን እና ከችግር መውጫ መንገድ አመላካችነቱን ማሳየቱን ነው የገለጹት፡፡ ለአማራ ሕዝብ ጦርነት አያስፈገውም፣ የአማራ ሕዝብ ጦርነት የሰለቸው ሕዝብ ነውም ብለዋል፡፡ ማንኛውም አካል መጨነቅ ያለበት ዜጎች እንዳይራቡ፣ እንዳይሳደዱ፣ እንዳይጎዱና ችግር ውስጥ እንዳይገቡ ማድረግ ላይ መኾን እንዳለበትም አመላክተዋል፡፡

የመጀመሪያውም የመጨረሻውም ተግባራችን የአማራ ክልል እና የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ ችግር እንዳይገባ ማድረግ መኾን አለበትም ብለዋል፡፡ የተጀመረው ሰላም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንደሚገባውም አንስተዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ በርካታ ጥያቄዎች እንዳሉት የተናገሩት አቶ ይርጋ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችን ይዘው እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች እንዳይመለሱ የሚያሰናክሉ ጉዳዮች መኖራቸውንም አመላክተዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄዎች መኾናቸውንም ነው ያስገነዘቡት፡፡

ዘመኑን የሚዋጅ የትግል ሥልት የአማራን ሕዝብ ጥያቄዎች እንደሚያስመልሳቸውም ገልጸዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች እንዲመለሱ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ትግሎች ያስፈልጋሉ ብለዋል፡፡ የሚደረገው ዴሞክራሲያዊ ትግል ሁሉንም ክልሎች ያሳተፈ መኾን አለበት ነው ያሉት፡፡ የአማራ ሕዝብን ሥነ ልቦና የሚመጥን፣ ጥያዌችን የሚመልስና የሚታገል መዋቅር እየተደራጀ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ ከችግር እንዲወጣ መስዋእት ኾነው የሠሩ መሪዎች እንደነበሩም ገልጸዋል፡፡ የመዋቅር መደራጀቱ እስከታችኛው መዋቅር ይካሄዳል ነው ያሉት፡፡ መሪ መለየትና ማደራጀት የክልሉን ሕዝብ የልማትና ሌሎች ጥያቄዎችን ለመመለስ እድል እንደሚሰጥም ገልጸዋል፡፡ ሕዝቡን የሚመጥን መዋቅር መፍጠር የመጀመሪያው ሥራችን ነውም ብለዋል፡፡ ከፖለቲካ መዋቅሩ ባሻገር የጸጥታ መዋቅሩን የመለየት፣ የማደራጀት እና የማሰልጠን ተግባር ይከናወናል ነው ያሉት፡፡ የጸጥታ መዋቅሩን የማደራጀት ሥራ እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ሕዝቡ የደረሰበትን ችግር፣ ለሕዝቡ ያላደረግናቸውን ግን ደግሞ ማድረግ የሚገባንን ለማድረግ የሚያስችል መዋቅር መፍጠር ይገባል ነው ያሉት፡፡ ለአማራ ሕዝብ የሚጠቅም ሥራ መሥራት ግድ እንደሚልም አመላክተዋል፡፡

ለችግር በሚቀመጡ መፍትሄዎች ዙሪያ ከሕዝብ ጋር መወያየት እና መግባባት የማይታለፍ ጉዳይ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ሰላም እንዲሰፍን፣ ሰላም ሰፍኖ ሕዝቡ የልማት ተጠቃሚ እንዲኾን ከተፈለገ ሕዝቡን በሁሉም ነገር ባለቤት ማድረግ ይገባልም ብለዋል፡፡ በክልሉ ተደጋጋሚ ውይይቶችን ለማድረግ እየተዘጋጁ መኾናቸውን የተናገሩት አቶ ይርጋ አሁን እየተደረጉ ያሉ ውይይቶች በቂ አለመኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ከችግሮቹ በዘላቂነት ለመውጣት ከሕዝብ ጋር ውይይት ማድረግ አስፈላጊ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡

የሀገር መከላከያ ሠራዊት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት አያሌ መስዋእትነት እንደከፈለና ለአማራ ሕዝብ ክብር መጠበቅ እልህ አስጨራሽ ትግል ማድረጉንም አስታውሰዋል፡፡ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ልዩ ክብር መስጠትና መጠበቅ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ ሠራዊቱ ሁልጊዜም ያስፈልጋል፣ የኢትዮጵያ ምልክት ነውም ብለዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ የሰላም ዘብ ነው፣ ለሰላም የቆመ ነው ያሉት ኀላፊው የአማራን ሕዝብ ጥያቄ መፍታትና ሰላሙን ማስፈን እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ ሰላም ከማስፈን ባለፈ ልማት የሚያለማ መዋቅር እያደራጁ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ለልማት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠርና ሕዝቡ ያጣውን ልማት እንዲያገኝ ሰላም ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ ሕዝብን በልማት የሚክስ ሥራ ለመሥራት ሁሉም አካል ተሳታፊ መኾን አለበት ብለዋል፡፡

ሕዝቡ እየገጠመው ያለውን ችግር በቅደም ተከተል እየፈታን ከሄድን አቅማችን እየኾነ ይሄዳል ነው ያሉት፡፡ የሚታይ የሚጨበጥ ውጤት ለማምጣት የሕዝብን እንባ ማበስ አለብንም ብለዋል በመግለጫቸው፡፡ የብልጽግና አባላትና ደጋፊዎችም ሕዝብን የሚጠቅም ሥራ መሥራት እንደሚገባቸውም ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ወጣቶች ልክ እንደስካሁኑ ሁሉ በጥልቀት በማሰብ፣ በማንሰላሰል እና ነባራዊ ሁኔታውን በመረዳት ሰላም እንዲሰፍን፣ በክልሉ ያለው የልማት እጦት እንዲያገግም እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የወጣቶችን ጥያቄ ለመመለስ ቀጣይ በርካታ ሥራዎች ይጠበቁብናልም ነው ያሉት፡፡ ከውጭም ከውስጥም ነገሮች ተቀነባብረውበት በችግር ውስጥ ያለውን ክልል ወደ ሰላም ለመመለስና ችግሮቹን በመመከት በኩል የወጣቶች ሚና ላቅ ያለ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ የጸጥታ መዋቅሩ ዋነኛ ተልእኮ የሕዝብን ሰላም መጠበቅ ነው ያሉት አቶ ይርጋ ሕዝቡ በችግር ውስጥ እንዳይቀጥል የጸጥታ መዋቅሩ መሪ ኾኖ መተግበር ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ የጸጥታ መዋቅሩ ለሕዝቡ የሚከፍለውን መስዋእትነት ሁሉ ለመክፈል መዘጋጀት እና በአንድነት መቆም እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ጠንካራ የፖለቲካና የጸጥታ መዋቅር መፍጠር የመጀመሪያው ተልእኳቸው መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችን መመለስ የማይታለፍ ተግባር ነውም ብለዋል፡፡ ጠንካራ፣ አስተዋይ እና ለሰላም የሚቆም ሕዝብ ነው ያለን ያሉት አቶ ይርጋ ሕዝቡን ይበልጥ ጠንካራ እንዲኾን ከእኛ ብዙ ተግባር ይጠበቃልም ብለዋል፡፡ በአማራ ክልል ሰላምና ልማት እንዳይኖር የሚያደርግን አካል መለየትና በሕግ ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ ሁሉም የሚችለውን ካደረገና ከሠራ ሰላማዊ እና በልማት ከፍ ያለ ክልል እንፈጥራለን ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጥላቻ እና ክፋትን በማስወገድ በምትኩ በጎነትን ልንተክል ይገባል” ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ
Next article“በጎነት እንደ ሀገር መተሳሰብ፣ መረዳዳትና ማኅበራዊ ፍትሕ እንዲሰፍን ሚናው የላቀ ነው” ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይ