“ጥላቻ እና ክፋትን በማስወገድ በምትኩ በጎነትን ልንተክል ይገባል” ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ

158

ባሕር ዳር: ጳጉሜን 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዛሬ ጳጉሜን 3 “የበጎነት ቀን” በሚል መርሃ-ግብር በባሕር ዳር ከተማ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል። በመርሃ-ግብሩ ላይ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ የክልል ከፍተኛ የመንግስት ሥራ ኃላፊዎች ተገኝተው የበጎነት ቀንን በማስመልከት ለአቅመ ደካማ ወገኖች ማዕድ አጋርተዋል።

በመርሃ-ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ርዕሰ መሥተዳድሩ፤ ጥላቻ እና ክፋትን በማስወገድ በምትኩ በጎነትን ልንተክል ይገባል ይገባል ብለዋል። የበጎነት ቀን እየተከበረ ያለውም ለሰው ልጆች መልካም የማድረግ ልማዳችንን ለማሳደግ እና ለማስቀጠል መሆኑን ገልፀው ጥላቻን፣ ክፋትን፣ ስግብግብነትን፣ ለብቻ መኖርን በማስወገድ ከግፉዓን ጋር በተግባር ለመገናኘት እና ለመደጋገፍ ታስቦ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በሀገራችን ኢትዮጵያ በጎነት ትልቅ ዋጋ እንደሚሰጠው የገለፁት ርዕሰ መሥተዳድሩ ሃይማኖታዊ እና ግብረ-ገባዊ ዕሴትነቱ አብሮን የመጣ ቢሆንም ከጊዜ ወደጊዜ እየደበዘዘ መምጣቱን አስታውሰዋል። ይሁን እንጂ የቆየውን የበጎነት ዕሴት በማጎልበት ይበልጥ መተሳሰብ እና መደጋገፍ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በቁስ ከመደጋገፍ እና ከመተጋገዝ በተጨማሪም በሀሳብ ጭምር በማገዝ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚታዩ ችግሮችን መቀነስ ይገባልም ነው ያሉት።

የበጎነት ባህሉ እንዲጎለብት እና ዘላቂነት እንዲኖረው ተቋማዊ እና ማህበራዊ መሠረት እንዲይዝ ማድርግ እንደሚገባ የገለፁት ርዕሰ መሥተዳድሩ ይህን ለማድረግም ተቋማት፣ ረጅ ድርጅቶች፣ አደረጃጀቶች እና ግለሰቦች ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡ መንግስት የበኩሉን ድርሻ ለሚወጣም ጨምረው ገልፀዋል። መረጃው የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ነው።

ርዕሰ መሥተዳድሩ ከ200 በላይ ለሚሆኑ አቅመ ደካሞች ማዕድ ያጋሩ ሲሆን ከ30 በላይ ለሚሆኑ ረዳት ለሌላቸው እና አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች የዓመት የትምህርት ቁሳቁስ እና የደብተር መያዣ ቦርሳ ድጋፍ አድርገዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ልዩ ልዩ ሹመቶችን የሰጡ።
Next article”የአማራ ሕዝብ ሰላም ወዳድነቱን በተግባር አሳይቷል” አቶ ይርጋ ሲሳይ