
ባሕር ዳር: ጳጉሜ 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) እስኪ እራሳችንን እንጠይቅ? ማን ይኾን እንባ በግፍ ያልፈሰሰበት፣ ማን ይኾን እናት ያላለቀሰችበት፣ ማን ይኾን አባት ያላዘነበት፣ ማን ይኾን ሕጻናት ያልጠሉት፣ ማን ይኾን አረጋውያን ያልረገሙት፣ ማን ይኾን ቅን ልብ ያልተከፋበት፣ ማን ይኾን ስህተት ያልተገኘበት፣ ማን ይኾን ሐጥያት የሌለበት፣ ማን ይኾን በልቡናው ክፋትና ምቀኝነት ያልፈጠረበት፣ ማን ይኾን የሚያድግ ልጅ ያልጠላው፣ ማን ይኾን የሚሞት ሽማግሌ ያልረገመው፣ ማን ይኾን የሚያልፍ ዝናብ ያልመታው?
ደጋግ ልቦች እንባን በግፍ አያፈሱም፣ ቅን ልቦች እናት አያስለቅሱም፣ ሩህሩህ ልቦች አባት አያሳዝኑም፣ በሕጻናት አይጠሉም፣ በአረጋውያን አይረገሙም፣ የዋህ ልብን አያሳዝኑም፣ ከክፋትና ከክፉ አድራጊዎች ጋር አይተባበሩም፣ የክፋትን ነገር አያሳብቡም፣ በሚያድግ ልጅ አይጠሉም፣ በሚሞት ሽማግሌም አይረገሙም፡፡ ደጋግ ልቦች ክፋትን ይንቃሉ፣ ምቀኝነትንም ከልቡናቸው ነቅለው ይጥላሉ፣ መልካምነትን በልቡናቸው ማሳ ውስጥ ይተክላሉ፡፡ በሰውም በፈጣሪም የተወደደውን ያደርጋሉ፣ በክፉ ዘመን ተስፋን ያሳያሉ ፤ ሀዘን በበዛበት ጊዜ ደስታን ይፈጥራሉ፡፡ በሚያልፍ ዓለም የማያልፍ ሥራ ሠርተው ያልፋሉ ፤ በፈራሽ ገላ የማይፈርስ ታሪክ ይቀርጻሉ፡፡
ደጋጎች በግፍ የምትፈስ እንባን ያብሳሉ፣ የተከፋን ልብ ይጠግናሉ፣ የተቅበዘበዘችን ነብስ ያረጋጋሉ፣ የታረዘችን ገላ ያለብሳሉ፣ የተራበችን አንጀት ያጠግባሉ፣ የተጠማችን ጉሮሮ በውኃ ያረሰርሳሉ፣ መጠጊያ ያጡትን ያስጠጋሉ፣ የታመሙትን ይጠይቃሉ፣ የተጣሉትን ያስታርቃሉ፣ መልካም ዘርን በልቡና ላይ ይዘራሉ፡፡ በመልካም ማሳ ላይም መልካም ፍሬን ያሳያሉ፡፡
ደጋጎች የሌሎች ሐዘን ያሳዝናቸዋል፣ የሌሎች ቁስል ያማቸዋል፣ የሌሎች መከፋት ያስከፋቸዋል፣ የሌሎች መራቆት ያራቁታቸዋል፣ የሌሎች መራብ ይርባቸዋል፣ የሌሎች መጠማት ይጠማቸዋል፣ የሌሎች ስቃይ ያሰቃያቸዋል፣ የሌሎች መሳደድ እረፍት ይነሳቸዋል፣ የሌሎች የልብ መድማት ያደማቸዋል፤ ባለ ቅን ልቦች ወገናቸው እያዘነ እነርሱ ደስታን አይሹም፣ ወገናቸው ደጋፊ አጥቶ እነርሱ ተድላን አይናፍቁም፣ ወገናቸው እየተራበ እነርሱ ጠግቦ ማደርን አይፈልጉም፡፡ ወገኔን የበላው ጅብ ይብላኝ፣ ደስታዬም መከራዬም ከወገኔ ጋር ይሁን ይላሉ እንጂ፡፡
ደግ ልብ የተቸራቸው፣ ደግነትም የሚገዛቸው፣ የሰዎች መኖር የሚያስደስታቸው ሰው ናቸው፡፡ ለዓመታት ስጋቸውን አድክመዋል፤ ደስታና ምቾታቸውን ንቀዋል፣ ትተዋል፤ ረስተዋል፡፡ እርሳቸው የደከሙ አረጋውያን የሚመረኮዛቸው ምርኩዝ፣ አዕምሯቸው የታወከ የሚጠለሉባቸው ዋርካ፣ ሕጻናትን የሚያሳድጉ አባት ይኾኑ ዘንድ ለዓመታት ደክመዋል – የጯሂት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የአረጋውያን፣ አዕምሮ ሕሙማን እና የሕጻናት መረጃ በጎ አድራጎት ማኅበር መሥራችና ሥራ አሥኪያጅ ብርሃን መልካሙ፡፡
ስምን መላእክ ያወጠዋል ይሉት ግብር የተገለጠው እዚህ ላይ ነው፡፡ ብርሃን የተሰኙ ለብዙዎች ብርሃን የኾኑ በጎ አድራጊ፡፡
የጯሂት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የአረጋውያን፣ አዕምሮ ሕሙማን እና የሕጻናት መረጃ በጎ አደራጊ ማኅበር ጧሪ ቀባሪ ያጡ አረጋውያን የሚጠለሉበት፣ አሳዳጊ ያጡ ሕጻናት የሚያድጉበት፣ ሕመም የጸናባቸው ተጠልለው የሚኖሩበት ነው፡፡ ይህ በጎ አድራጎት ማኅበር የሚገኘው በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በምዕራብ ደንቢያ ወረዳ በጯሂት ከተማ ነው፡፡
ብርሃን በልጅነታቸው ጀምሮ ያዘኑ ሰዎች ያሳዝኗቸዋል፣ ደጋፊ ያጡ አረጋውያን ያስተክዟቸዋል፤ ያስለቅሷቸዋል፡፡ ገና እድሜያቸው ሳይጠና፣ የሚደገፉበት አቅምም ሳይኖራቸው መቼ ይኾን የተቸገሩትን የምረዳቸው? መቼ ይኾን የሚያዝኑትን የማጽናናቸው ? እያሉ ይመኙ ነበር፡፡
ደግ ያሰበ ደግ ይደረግለታል፣ ክፉም ያሰበ ክፉ ይሆንበታል እና የሚናፍቁት ጊዜ ደረሰ፡፡ ከልጅነት ጀምሮ የሚያስቡትን ሥራ እውን ያደርጉ ዘንድ ወደዱ፡፡ “ ነብስ ካወኩ ጀምሮ እዕምሮ ሕሙማንን፣ ረዳት የሌላቸው አረጋውያንን፣ አሳዳጊ ያጡ ሕጻናትን ሳይ አዝን ነበር፡፡ አቅሙ ባይኖረኝም ያሳዝኑኝ ነበር፡፡ እንዴት ሰው አያግዛቸውም? እያልኩ እጠይቅ ነበር፡፡ በኋላ የአረጋውያንን እግር ፣ ልብሳቸውን እያጠብኩ፣ እያጫወትኳቸው፣ ከማገኛት ጥቂት ብር እየከፈልኩ እየሰጠኋቸው መጣሁ፡፡ የምሰጠው ሳጣ በቤተክርስቲያን በስንበቴ እየዞርኩ እጠይቃለሁ፡፡ የሚሰጡኝን እያመጣሁ እሰጣቸዋለሁ፡፡ በኋላ የሰንበት ተማሪዎችን ለምን እየለመንን አናግዛቸውም ስል ጠየኳቸው፤ ፈቃደኛ ኾኑ፡፡ እሑድ እሑድ ቤተክርስቲያን፣ ቤት ለቤትም እየዞርን እየለመንን እንሰጣቸው ጀመር፡፡ ቀስ በቀስም ከፍ እያለ ሄደ” ነው ያሉኝ አጀማመራቸውን ሲያስታውሱ፡፡
ይህ በጎ ሃሳብ የተጀመረው በ1999 ዓ.ም ነው፡፡ በብርሃን ደግ ልብ ውስጥ የተዘራው ዘር በሌሎች ደጋግ ልቦች ላይም በቀለ፡፡ የተወደደውን ሀሳብ ወደዱት፡፡ የተቀደሰውን ሥራ ይሠሩት ዘንድ ወደዱት፡፡ እንደዋዛ የተጀመረው የበጎ ሥራ ወደ ተቋም ተቀየረ፡፡ ቆይቶም ሕጋዊ ዕውቅና አገኘና የበጎ አድራጎት ማኅበር ኾነ፡፡ በደጋግ ልቦች የሚረዱት ሰዎችም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ሄዱ፡፡ አሁን ላይ በዚያ በጎ አድራጎት ማኅበር ውስጥ 215 አረጋውያን፣ የአዕምሮ ሕሙማን እና ሕጻናት ይኖራሉ፡፡ የሃብታቸው ምንጭ በጎ ልብ፣ ቀና አስተሳሰብ ብቻ ነው፡፡ መልካም ያስባሉ፣ የልባቸውን መሻት አምላክ ይፈጽምላቸዋል፡፡ እርሱንም እያመሰገኑ ዓመታትን ይቀዳጃሉ፡፡ ጊዜያትን እያሳለፉ ጊዜያትን ይቀበላሉ፡፡ በጎ አድራጎት ማኅበሩ በአንድ ላይ ከያዛቸው ወገኖች አልፎ በየቤታቸው ኾነው የሚቸገሩ ወገኖችን ይረዳል፣ ልብሳቸውን ያጥባል፣ ካለው እያካፈለም ያጎርሳል፤ ያለብሳል፡፡
“የምንኖረው በቸርነቱ ነው፡፡ በጎነት ለስጋ ጥቅም የለውም፡፡ ስጋ ደስታን ትሻለችና፡፡ ለነብስ ግን ሀሴትን ይሰጣል፡፡ ሌላ ዓለም ውስጥ ያለሁ ይመስለኛል፡፡ ሕመማቸውን ስካፈል ሌላ ዓለም ውስጥ የምኖር ይመስለኛል፡፡ ደስተኛ ነኝ፡፡ ምን አበላቸው ይኾን የሚለው ጭንቀት ሊመጣ ይችላል፡፡ ግን እርሱም ደስታዬን አይወስደውም ደስተኛ ነኝ፡፡ ችግራቸውን ስንጋራ እርካታ ይሰማናል፤ ደስም ይለናል፡፡ በጎነት ውስጥ በገንዘብ የማይገዛ ደስታ አለ፡፡ በበጎነት ውስጥ ሰው ሊሰጥ የማይችል ደስታ አለ፡፡ ቀኑ መሽቶ እንደሚነጋ፣ ወራቶች እንዴት እንደሚያልፉ አይታወቀንም” ነው ያሉኝ፡፡
ለሌላ እየኖሩ፣ ለራስ እየተቸገሩ እና ደስታን እየናቁ መደሰት እንደ ምን ያለ ደስታ ነው? ሌሎችን እየደገፉ፣ ለሌሎችም ምርኩዝ እየኾኑ ሀሴት ማድረግ እንደምን ያለ መታደል ነው? ፈተናዎች ነበሩባቸው፡፡ በበጎ ሥራቸውም እንዳይቀጥሉ የሚያደርጉ አስቸጋሪ ፈተናዎችም ገጥመዋቸው ነበር፡፡ እርሳቸው ግን በጽናታቸው እና በአምላካቸው ረዳትነት ፈተናዎችን አልፈው ለብዙዎች ጥላ ለመኾን ምክንያት ኾኑ፡፡
“አሁን ሰውም መጥቶ ልገድልህ ነኝ ቢለኝም ፤ ከሥራዬ እንደማያነቃንቀኝ፣ ይሄን ሥራ እንደማያስተወኝ ይሰማኛል፡፡ ሰማያዊ ካልኾነ በስተቀር ምድራዊ ሰው ይሄን ሥራ እንደማያስተወኝ አምናለሁ፡፡ ራቁቴንም ሆኜ፣ በእስር ቤትም ሆኜ መልካም ነገር ለመሥራት የሚያግደኝ የለም” ብለውኛል፡፡ እርሳቸው በጎ አድራጎትን ከመሥራት የሚያስቆማቸው ነገር የለም፡፡ አማርሬ አላውቅም ነው ያሉኝ፡፡
“ብዙዎች ለራስህ ሠርተህ መኖር እየቻልክ ስለ ምን እንደዚህ ትኖራለህ ብለውኝ ነበር፡፡ እንቅፋቶችም ነበሩብኝ፡፡ ነገር ግን ከዚህ የሚበልጥ ነገር አላገኘሁም” ይላሉ ብርሃን፡፡ እርሳቸው ነብሳቸው ለበጎነት ተሰጥታለች፡፡ ልባቸውም መልካም ነገር ብቻ ታደርግ ዘንድ ተመርጣለች፡፡ ያንም እያደረገች ትኖራለች፡፡ ከበጎነት የሚያወጣትን ምክርም አትሰማም፡፡
“ሰው ሌሎችን ለመርዳት መጀመሪያ ሰው መኾን አለበት፡፡ ሰው አምላኩን መያዝ አለበት፡፡ በአልኮል ሱስ ኾነ በጫት ሱስ ተይዞና ራሱን እየጎዳ ፣ በስካርም መንፈስ ተይዞ በጎ ነገር ማድረግ አይቻለውም፤ ይሄን እኔ አምናለሁ፡፡
በጎነት ባለጸግነት ከመኾን የሚመጣ አይደለም፡፡ መንገድ የጠፋበትን ማመላከት በጎነት ነው፣ ዕውቀት የጠፋበትን ማሳወቅ በጎነት ነው፡፡ የተቸገረን አይዞህ ማለት በጎነት ነው፡፡ ያለንን ከፍሎ መስጠትም በጎነት ነው” ብለውኛል፡፡ በጎነት ከባዶ እንደሚጀመርም ነግረውኛል፡፡
አሁን ላይ ሀገሪቱ ባለችበት ሁኔታ ጠያቂ ጠፍቷል፡፡ ጠያቂዎች ከጠፉብን፣ ወገኖቻችን ይራቡብናል፡፡ እስካሁን ያለችንን እየቆጠብን ነው እየኖርን ያለነው፣ ግን አምላክ ይመስገን በቸርነቱ እንኖራለን ነው ያሉኝ፡፡ በሀገር ውስጥም ኾነ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እንዲያደርጉላቸውም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ አሁን ላይ አጋዥ ጠፍቷልና አትርሱን ፤ በጎ አድርጋችሁ የተወደደውን ነገርም ከአምላክ ዘንድ ታገኛላችሁ፣ በጎነት በሰውም በአምላክ ዘንድም ክብርን ያሰጣል ነው ያሉኝ፡፡
እጆቻችሁ በጎን ያድርጉ፣ ጀሮዎቻችሁ በጎ ነገርን ያድምጡ፣ ዓይኖቻችሁ በጎ ነገርን ይመልከቱ፡፡ ልባችሁ በጎ ነገርን ያስብ፡፡ በጎ ባደረጋችሁ ጊዜም ምድር ትረጋጋለች፣ ረሃብና ቸነፈር፣ ጠብና ብጥብጥ ትጠፋለች፡፡ ሰላምና ፍቅር፣ ተድላና ደስታም ትሰፋለች፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!