
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ባለታሪኳ ገነት ተመሰገን ትባላለች። ነዋሪነቷ በባሕርዳር ከተማ ነው። አንድ ቀን ለሥራ ተቻኩላ ታክሲ ላይ ተሳፈረች። ገነት ከታክሲ ወርዳ ስልክ ለመደወል ስትፈልግ ሞባይሏን ከእጇ አጣችው። ቦርሳዋን ፈተሸች፤ ኪሷን በረበረች። በውድ ዋጋ የገዛችው ስልኳ የለም።
አሳፍሮ ያመጣትን ታክሲ ለማፈላለግ ከወረደችበት ቦታ ወደ ፊት ገሰገሰች። የቆየችበትን ታክሲ ፍለጋ ተያያዘች። ታክሲው አልተገኘም። በውድ ዋጋ የተገዛው ስልኳ ጠፍቶ መቅረቱ ቁርጥ ኾነ።
በውድ ገንዘብ የተገዛው ሞባይል በገንዘብ ሊገዙ የማይችሉ የገነትን ውድ መረጃዎች ይዞ ነው የጠፋ። ለዓመታት የተጠራቀሙ የጽሑፍም የምስልም መረጃዎቿን ነው ያጣች። ሞባይሉን መልሳ የምታገኝበት ምንም አይነት መንገድ አለመኖሩንም ተረዳች። ተስፋ ቆርጣም ወደ ዕለቱ ሥራዋ አቀናች።
ከሦስት ቀናት በኋላ አራት የጎዳና ልጆች ከመሥሪያ ቤቷ በር ላይ እንደሚፈልጓት በባልደረባዋ ይነገራታል። “ደግሞ ምን ቸገራቸው ይኾን” እያለች ወደ በሩ አቀናች።
ርሃብ እና እርዛት ላያቸው ላይ የሚነበብ አራት የጎዳና ልጆች ውድ ዋጋ የሚያወጣውን የገነትን ስልክ ይዘው ጠበቋት። ይኾናል ብላ ያላሰበችው ነገር ስለኾነ ደነገጠች።
ሞባይሉን በእጁ የያዘው ልጅ “ይሄው ሦስት ቀን ሙሉ አንችን ፍለጋ ስንከራተት ነው የሰነበትን” አለና ሰጣት። ስልኩን ከእጁ ፈጥና ተቀበለችና በስልኳ ስክሪን ሴቨር ላይ ያስቀመጠችውን የራሷን ፎቶ አተኩራ እያየች የት እንዳገኙት ጠየቀቻቸው።
ስልኩን የሰጣት ልጅ “እኛን ግን አላስታወስሽንም? ከሌሎች ሰዎች ጋር ኾነሽ በተለያየ ጊዜ ልብስ ሰጥተሽናል እኮ፣ እስካሁን ድረስ እናንተ የሰጣችሁንን ልብስ ነው ሌሊት ለብሰን የምንተኛ” አላት።
ሌላኛው ጓደኛው አከታትሎ “እትጌ ስልክሽን ያዥ፣ ያኔ ከቦርሳሽ ተንሸራትቶ ሲወድቅ ከጎንሽ እኔ ነበርሁ። ሸጠን ዳቦ እንገዛበታለን ብየ ይዤው ብሄድም ጓደኞቸ ፎቶሽን አይተው አወቁሽ፣ ያንችን ስልክ መሸጥ ስለማንችል ነው አድራሻሽን አፈላልገን ያመጣንልሽ” አላት።
ገነት በባሕርዳር ከተማ የሚገኘው የድንበርየለሽ በጎ አድራጎት ማኅበር ምክትል ሥራ አስፈጻሚ በመኾን በከተማው የተለያዩ በጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ የምትሳተፍ ወጣት ናት። የገነት የቀደመ በጎ ሥራ ላይገኝ የጠፋውን ውድ ሞባይሏን እና በገንዘብ የማይተመኑ መረጃዎቿን መለሰላት። በገነት እና ጓደኞቿ ምክንያት ደግ ነገር የተደረገላቸው እነዚህ የጎዳና ልጆች በስልኳ ላይ የተቀመጠውን ፎቶዋን አይተው ስላወቋት ነው የጠፋ ንብረቷን ካለችበት ድረስ ተጉዘው የመለሱላት። “ደግነት ለራስ ዞሮ ይከፍላል” ብላለች ገነት።
የዛሬው ቀን በጎነትን የምናስብበት መጭው አዲስ ዓመት ደግሞ በጎ ነገሮችን የምንሠራበት እንዲሆን ተመኘን!
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!