
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በጎነት በእድሜ የሚገደብ ባይኾንም ወጣቶች በአፍላ ጉልበትና እውቀት የሚያከናውኑት መልካም ተግባር ጎልቶ የሚታይበት መሆኑን ያለፉት አምስት ዓመታት ማሳያዎች መኾናቸውን የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ እርዚቅ ኢሳ ገልጸዋል። ባለፋት አምስት ዓመታት 25 ሚሊዮን ወጣቶች በድግግሞሽ በበጎ ተግባር ተሳትፈዋል፤ በዚህም ከ32 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የመንግሥት ሀብትን ማዳን ተችሏል ብለዋል።
ኀላፊው እንዳሉት በዚህ ዓመት በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች 437 ሚሊዮን ችግኝ ተተክሏል፤ 1 ሺህ 91ዐ አዲስ የአረጋውያን ቤቶች ተገንብተዋል፤ ከ2 ሺህ 900 በላይ ነባር የአረጋውያን ቤቶች ተጠግነዋል፤ 6 ሺህ 610 ዩኒት ደም በወጣቶች ተለግሷል፤ በ514 ትምህርት ቤቶች ደግሞ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት ተሰጥቷል።
በዚህ ወቅትም ቢሮው የበጎነት ቀንን አስመልክቶ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ለአረጋውያን ድጋፍ ማድረጉን ገልጿል። በባሕርዳር ከተማ አሥተዳደርም ለታዳጊ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ እና ለአረጋውያን ደግሞ የዘይትና ፊኖ ዱቄት ድጋፍ አድርጓል።
ሌሎች ወገኖችም ሀገራቸውን ላገለገሉ ጧሪ እና ደጋፊ ለሌላቸው አረጋውያን እና በቀጣይ ሀገር ተረካቢ ለኾኑ ሕጻናት ድጋፍ የማድረግ ባሕልን ማዳበር ይገባል ብለዋል።
የተደረገው ድጋፍ እንደማንኛውም ሰው በዓልን በደስታ ለመዋል እንደሚያስችላቸው ድጋፍ የተደረገላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ገልጸዋል። በበዓላት ወቅት በበጎ ፈቃደኞች የሚደረገው ድጋፍ በዘላቂ ሥራ ለመሠማራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይም ትኩረት ቢደረግ ከጥገኝነት መላቀቅ እንደሚቻል ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!