
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) መቄዶንያ የተሰኘ የአረጋዊያን መርጃ ማዕከል የተሰኘ የበጎ አድራጎት ማኅበር በመመስረት በመላው ኢትጵያዊያን ልብ ውስጥ ገብቷል ቢኒያም በለጠ።
በ 1970ዓ.ም ከእናቱ ጽጌ በቀለ እና ከአባቱ በለጠ አዲስ በአዲስ አበባ የተወለደው ቢኒያም በለጠ ለቤተሰቦቹ 6ኛ ልጅ ሲኾን በትምህርቱም ምስጉን የሚባል ነው። አራት ነጥብ በማስመዝገብ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቅሎ ሕግ በማጥናት ለሦስት ዓመታት በሕግ ባለሞያነት በሀገር ውስጥ አገልግሏል።
ቢኒያም በትምህርት ዓለም ስኬታማ ቢኾንም በውስጡ የሚያረካው እና እረፍት የሚሰጠው ኾኖ ግን አላገኘውም።
ቢኒያም በመንገዱ ላይ ወድቀው አጋዥ ያጡ ሰዎችን እያየ ልቡ ይሰበር ነበር። በምን መንገድ ሊያግዛቸው እንደሚችል ሁሌም ያወጣል ያወርዳል።
በዚህ ሂደት ታዲያ ወደ ሀገረ አሜሪካ ተጓዘ፡፡ እዚያም የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቶ ሁለተኛ ዲግሪውን በነን ፕሮፊት ማኔጅመንት ኤንድ ዴቨሎፕመንት ተምሮ ተመረቀ።
በዚህ ሂደትም ሀገሩ ያለው ሁኔታ ሁሌም ያሳስበዋል። “ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው” በሚለው መሪ ቃሉ የምናውቀው ቢኒያም የአረጋውያን መጦሪያ ማጣት ከዚያም በላይ በየመንገዱ መውደቅና ጧሪ ቀባሪ ማጣት ሀሳቡ አይሎ በሀገረ አሜሪካ የተማረውን እውቀት እና ያጠራቀመውን ገንዘብ ይዞ አስታዋሽ ላጡ ሊደርስ የቅንጦት እና የምቾት ሕይወቱን ትቶ ወደ ሀገሩ ለመመለስ ግድ አለው፡፡
እንደተመለሰም በ1992/93 ዓ.ም መቄዶንያ የተሰኘ የአረጋዊያን መርጃ ማዕከልን በመክፈት 20 ደጋፊ ያጡ ሰዎችን በወላጆቹ ቤት ማኖር ጀመረ፡፡
መቄዶንያ አሁን ትልቅ የሰብአዊ እርዳታ አገልግሎት መስጫ ኾኖ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ያግዛል።
ቢኒያም አጋዥ ለሌላቸው እንዲሁም የአካል ጉዳት ላለባቸው አረጋውያን ድጋፍ እየሰጠ ነው፡፡
ቢኒያም በኢትዮጵያ ካሉ በጎ ሰዎች ውስጥ አንዱ ነው፤ በሱ መኖር የብዙዎች ሕይወት ተቃንቷል። በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በዘመናቸው ማምሻ ላይ እንባቸው ታብሷል።
ቢኒያም ለሌሎች አርአያ የሚኾን ኾኖ በማግኘቱ በበጎ ሥራው ከአንጋፋዎቹ ከባሕር ዳር ዩኒቨርስቲእና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት ተሰጥቷል።
እኛም ቢኒያም በለጠ በዛሬው የበጎ ሰው ቀን ሊመሠገን የሚገባው ኾኖ አኘነው። ምሥጋናችንም ይድረስህ እንላለን።
በምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!