“ሀገራዊ ምክክሩ የተረጋጋችና የምንፈልጋትን ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት ትልቅ መደላድል ለመፍጠር አጋዥ እንደሚሆን ትልቅ እምነት አለን” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

54

ባሕር ዳር: ጳጉሜን 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አባላት ጋር ምክክር አድርገዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በተፈጠሩ የተሳሳቱ ትርክቶች በሕዝብ አንድነት ላይ አደጋ የሚጥሉ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል። የአማራ ሕዝብም የተሳሳቱ የፖለቲካ ትርክቶች ታርመው በምክክር ወደተሻለ ሀገረ መንግሥት ግንባታ እንዲገባ በተለያዩ አጋጣሚዎች እያነሳ መቆየቱንም አንስተዋል።

በኢትዮጵያ በየጊዜው የሚፈጠሩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በማለም የተቋቋመው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሊያካሒድ ያለመው ምክክር የተረጋጋችና የምንፈልጋትን ጠንካራ ኢትዮጵያ ለመገንባት ትልቅ መደላድል ለመፍጠር አጋዥ እንደሚሆን ትልቅ እምነት አለን ብለዋል ርእሰ መስተዳድሩ።

የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተከብረው በአብሮነት የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሚደረገው የምክክር ሒደት በውጤታማነት እንዲከናወንም የክልሉ መንግሥት ምቹ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥርም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ተገኘወርቅ ጌጡ (ዶ.ር) በበኩላቸው ባለፉት 2 ዓመታት ገደማ ኮሚሽኑን በሰው ኀይል ከማደራጀት ጀምሮ ለሀገራዊ ምክክሩ በአጀንዳነት የሚመረጡ ርእሰ ጉዳዮችን እያሰባሰቡ መሆኑን ተናግረዋል። በተለያዩ ክልሎች የተሳታፊ ልየታ ሒደት መጀመሩን የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ እስካሁን 60ሺ የሚጠጉ ሰዎችን ማወያየት መቻሉን አስታውቀዋል።

በአማራ ክልል በየወረዳው 7 ተባባሪ አካላትን እንፈልጋለን ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ከዘጠና እስከ አንድ መቶ ሰዎችም ይለያሉ ነው ያሉት። ሊካሔድ በታሰበው የምክክር ሒደት የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ግብዓት እንዲያመቻች ጠይቀዋል።

የአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አባላት ጋር ያደረጉት ውይይት የምክክሩ ተሳታፊዎችን ለመለየትና ለውይይቱ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር መደረግ ስላለባቸው ቀጣይ ተግባራት ዙሪያ ሰፊ ምክክር የተደረገበት ነው።

ዘጋቢ፦ ስማቸው እሸቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የፓስፖርት አሰጣጥ አገልግሎት ተቋርጦ የነበረው በፓስፖርት ምርት እጥረት እና ቢሮው እየሠራ ባለው አዲስ የመዋቅር ጥናት ላይ ስለነበር ነው” የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት
Next articleዛሬ ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር ትጫወታለች።