
አዲስ አበባ: ጳጉሜ 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ)የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ከወራት በፊት ወደ አዲስ አሠራር እና አመራር ወደ ሥራ በመግባቱ እንደኾነ ተገልጿል። ተቋሙ በአዲሱ አሠራር የተከናወኑ ሥራዎችን እና የቀጣይ እቅዶችን በሚመለከት መግለጫ ሰጥቷል።
የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ላለፉት 6 ወራት የፓስፖርት አገልግሎት ያልተሰጠባቸውን ምክንያቶችም በሚመለከት የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ለተጠቃሚዎች የፓስፖርት አሰጣጥ አገልግሎት የተቋረጠው የፓስፖርት ምርት እጥረት በማጋጠሙ እና ቢሮው በአዲስ መዋቅር የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ ጥናት በማድረግ ላይ ስለነበረ መኾኑን ዳሬክተሯ ተናግረዋል።
ቢሮውን በአዲስ መዋቅር እና አሠራር ለማዋቀር የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ በነበሩ ጥናቶች ተቋሙ ክፍተቶቹን ለይቷል ብለዋል ወይዘሮ ሰላማዊት።
የተገኙ ችግሮችንም ሲያብራሩ:-
👉 የፓስፖርት ምርት እጥረት
👉 የቴክኖሎጅ አጠቃቀም ጉድለት
👉 የኦንላይን አጠቃቀም ችግሮች
👉 የደላሎች መበራከት እና የተገልጋዮች መጭበርበር
👉 ቢሮው በቴክኖሎጅ አጠቃቀም የበለፀገ ባለመኾኑ የፓስፖርት እና የቪዛ አሰጣጥ አለመፍጠን የታዩ ችግሮች መኾናቸውን ጠቅሰዋል።
በቀጣይም በአጭር ፣ በመካከለኛና በረጅም እቅዶች አሠራሮችን በማስተካከል ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት መታቀዱ ተጠቅሷል።
የፓስፖርት ምርት እጥረትን ለመቀነስም ከአምራች ድርጅቶች ጋር በመነጋገር 190 ሺህ ፓስፖርት ምርት ወደ ሀገር መግባቱ ነው የተገለጸው።
የፓስፖርት አገልግሎትን ለ6 ወራት ለጠበቁ ዜጎችም በቀጣይ ፓስፖርት በማተም እንደሚሰጥም አስገንዝበዋል።
ቪዛን በሚመለከት የታዩ ጉድለቶችን ለመቅረፍም እቅድ ተይዞ እየተሠራበት መኾኑን ዳይሬከተሯ ጠቅሰዋል።
ማኅበረሰቡም ሕጋዊ የኾነ አገልግሎትን ለማግኘት ከተበራከቱ ደላሎች ሊጠበቅ እና ደላሎችን ሊያጋልጥ እንደሚገባም መልእክት አስተላልፈዋል።
ፓስፖርት በ90 ቀናት ውስጥ ያለፋቸው ተገልጋዮችም ቅዳሜ ቅዳሜ አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉም ጠቅሰዋል።
ዘጋቢ:- ራሄል ደምሰው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!