“መጀመሪያችንም መጨረሻችንም የሕዝብ ሰላም መኾን አለበት” አቶ ይርጋ ሲሳይ

53

ባሕር ዳር: ጳጉሜ 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ)በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በአማራ ክልል የተፈጠረውን የሰላም እጦት ለመፍታት በተሠሩ ሥራዎች አንፃራዊ ሰላም እየተፈጠረ ሰላሙ እየተሻሻለ እንደሚገኝም ገልጸዋል። የአማራ ክልል በባሕሪው ብዙ ውስብስብ ችግሮች የሚፈጠሩበት ፤ በውስጥም በውጭም ባለው ጫና ችግሮች የሚበረክቱበት መኾኑንም ነው የተናገሩት።

ከሰሜኑ ጦርነት ማግሥት በርካታ ታጣቂዎች እንደተፈጠሩ ያነሱት አቶ ይርጋ ታጣቂዎቹ ወደ መደበኛ ሕይወት እንዲመለሱ ፣ በመንግሥት የፀጥታ መዋቅር እንዲካተቱም ብዙ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል። ብዙዎችም እድሉን መጠቀማቸውን ነው የገለጹት። አንዳንዶቹ ግን የተሰጣቸውን እድል ባለመጠቀም ወደ ግጭት መግባታቸውን ተናግረዋል። ከጊዜ ወደጊዜ የፀጥታው ኹኔታ ሲባባስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁንም አስታውሰዋል።

አስቸኳይ ጊዜ በመታወጁና በቅንጅት በመሠራቱ በክልሉ አንፃራዊ ሰላም ተፈጥሯል ነው ያሉት። ዜጎች ሰላም እንዲያገኙና ማኅበራዊ ሕይወታቸውን እንዲከውኑ ማድረግ ይገባል ብለዋል። በክልሉ የመጣው የሰላም ለውጥ ትልቅ መኾኑንም ተናግረዋል።

ሕዝቡ ሰላም መፈለጉ ፣ ጦርነትን በመሰልቸቱ በፍጥነት ሰላም መመለሱንም ገልጸዋል። የአማራ ሕዝብ ሰላም እንዲቀጥል ፤ ግጭት እንዲቆም የተሠራው ሥራ ታሪክ የማይረሳው ፤ የአማራን ሕዝብ ሥነ ልቦና የሚመጥን ነው ብለዋል። ሕዝቡ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውም አመላክተዋል። አሁን ሕዝቡ በጀመረው አግባብ ከሄደ በአጭር ጊዜ ወደ ፍጹም ሰላም መመለስ ይቻላልም ነው ያሉት።

የአማራ ሕዝብ ሀገር በተቸገረች ጊዜ ሁሉ ቀድሞ የሚደርስ መኾኑን የተናገሩት ኀላፊው አሁንም ሥነ ልቦናውን የሚመጥን የሰላም ሥራ መሠራቱንም ተናግረዋል። ፖለቲከኞችም ኾነ ሌሎች አካላት ለዜጎች ሰላም መሥራት አለባቸው ፤ ከአባባሽ ነገሮች መራቅ አለባቸው ነው ያሉት። መጀመሪያችንም መጨረሻችንም የሕዝብ ሰላም መኾን አለበትም ብለዋል። አሁን ላይ ክልሉ ከችግር እየወጣ መኾኑንም ተናግረዋል።

የአማራ ሕዝብ በርካታ ጥያቄዎች አሉት ፤ ለውጥ የመጣውም ጥያቄዎችን መሠረት አድርጎ ነው ያሉት አቶ ይርጋ ጥያቄዎችንም ለመመለስ እየሠራን ነው ብለዋል። የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች የሚመለሱት በዲሞክራሲ እንጂ በአፈሙዝ እንዳልኾነም አንስተዋል። የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ ከተፈለገ በዲሞክራሲ አግባብ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።

የአማራ ሕዝብ መታገል ያለበት ጥያቄዎቹ እንዲመለሱለት ነው ፤ ጥያቄዎቹ እንዲመለሱለት ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር መታገል አለበትም ብለዋል። የክልሉን ሰላም በአስተማማኝ ኹኔታ ለመመለስ በርካታ ሥራዎች እንደሚያስፈልጉም ገልጸዋል። ክፍተቱን ለመሙላት ክልሉን የሚመጥን የሕዝቡን ሥነ ልቡና እያየ ጥያቄዎችን መመለስ የሚያስችል መሪ ማደራጀት ስላስፈለገ መሪዎችን የማደራጀት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።

ከክልሉ ጀምሮ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ መልሶ ይደራጃልም ብለዋል። ሕዝብን የሚመጥን መሪ የመፍጠር ሥራው የመጀመሪያው ተግባር መኾኑንም አንስተዋል። አመራር የመለየትና የማደራጀት ሥራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ነው ያሉት። ክልሉና ሕዝቡን የሚመጥን መዋቅር መፍጠር ግድ ነው ብለዋል። ወቅቱን የሚመጥን ፣ ሕዝብን የሚያገለግል ጠንካራ አመራር መፍጠር አስፈላጊ መኾኑንም አንስተዋል።

የጸጥታ መዋቅሩን ማደራጃት ሌላው ተግባር መኾኑንም ገልጸዋል። ለውጡ እጅግ አጓጊ እና ሕዝብ የተቀበለው እንደነበር ያነሱት ኀላፊው ከለውጡ በፊት የነበሩ ውስብስብ ችግሮች ለውጡን በተፈለገው ልክ እንዳይሄድ እንዳደረገውም ገልጸዋል። ከሕዝብ ጋር መግባባትና በሁሉም ነገር ሕዝብን ባለቤት ማድረግ ወሳኝ ነውም ብለዋል።

ከሕዝብ ጋር መወያየት ፣ በግልፅ መነጋገርና መግባባት የማይታለፍ ተግባር መኾኑንም አስታውቀዋል። አሁን ያለው ግጭት የአማራን ሕዝብ የማይመጥን መኾኑንም ተናግረዋል።

የአማራ ሕዝብ ከግጭት ወጥቶ የተጠማውን ልማት ማግኘት አለበትም ብለዋል። ወደ ልማት ሳይገባ ኢኮኖሚን ማሳደግ ሳይቻል ጥያቄዎችን መመለስ አይቻልም ነው ያሉት። ለአማራ ሕዝብ የተጠማውን ልማት መስጠት ግድ እንደሚልም ተናግረዋል።

በአንድ በኩል ሰላምን መጠበቅ ፣ በሌላ በኩል ደግሞ አዳዲስ የልማት ሥራዎችን መሥራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። ሕዝቡን እያማረሩ ያሉ የመልካም አሥተዳደር ችግሮች መፈታት አለባቸውም ብለዋል። መፍታት ሲገባን ያልፈታናቸው ችግሮች እየበዙ በመምጣታቸው ሕዝቡ ተቀይሞናልም ነው ያሉት። ከላይ እስከታች ያለው መዋቅር ከጥላቻ ነፃ ኾኖ ለአካባቢው ሰላምና ልማት መጨነቅ ፣ የሕዝብ እንባ ማበስ አለበት ብለዋል።

መፍታት የሚገባንን ሳንፈታ ከሄድን ሕዝብን እያስቀየምን እንሄዳለን፣ ሕዝብ ሲቀየም ደግሞ ለአመራር እንቸገራለን ነው ያሉት። አዳዲስ መሪዎችም ኾነ በሕዝብ ታምኖባቸው የሚቀጥሉ መሪዎች ለሕዝብ ጥቅም መሥራት አለባቸው ነው ያሉት።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በጎ ሀሳብ ያለው ሰው ለሌሎች የሚሰጠው ነገር አያጣም” የድንበር የለሽ በጎ አድራጎት ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ ወጣት ምሕረት ታከለ
Next article“የፓስፖርት አሰጣጥ አገልግሎት ተቋርጦ የነበረው በፓስፖርት ምርት እጥረት እና ቢሮው እየሠራ ባለው አዲስ የመዋቅር ጥናት ላይ ስለነበር ነው” የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት