
ባሕር ዳር: ጳጉሜ 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዛሬ ጳጉሜን 3 በበጎነት ቀን ታስቦ፣ የበጎነት ሥራም እየተከናወነበት ይውላል።
ኢትዮጵያ ከራሳቸው በፊት ለወገን የሚያስቡ በጎ ሰዎች የማይነጥፉባት ሀገር ናት። አንድ በበጎ ሥራ ላይ የተጠመደ ሰው ልናስተዋውቃችሁ ነው።
ስሙ ምሕረት ታከለ ይባላል። ድንበር የለሽ የበጎ አድራጎት ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ ነው። የትወና ረዳት መምህርም ነው። ማኅበሩን የተቀላቀለው በ2010 ዓ.ም ነው። የእነምሕረት ማኅበር መሪ ሃሳብ “በጎ እናስብ” የሚል ነው። በዚህ ማኅበር ውስጥ ከሚገኙ አቻዎቹ ጋር ኾኖ በርካታ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ያከናውናል።
ምሕረት ከእጁ የተትረፈረፈ ገንዘብ ባይኖረውም ሌሎችን ለማገዝ ግን ብቁ መኾኑን ነግሮናል።
አልባሳትን ከሌሎች ሰዎች በማሰባሰብ ለበርካታ የጎዳና ልጆች አልብሶ ከእርዛት አድኗል። በሱስ ውስጥ ያሉ ሰዎቹ ከያሉበት እየፈለገ ወደ ትክክለኛ መንገድ እንዲጓዙ ለማስቻል እየተንቀሳቀሰ ነው። መጽሐፍትን አሰባስቦ ለወጣቶች በማድረስ ከሱስ ይልቅ ወደ ንባብ እና ዕውቀት እንዲያዘነብሉ የበኩሉን እየተወጣ ነው። ወጣት ምሕረት የአቅመ ደካማዎችን ቤት በመጠገን፣ ከተማን በማጽዳት፣ በዓላትን ከተቸገሩት ጋር በማሳለፍ እና በሌሎችም በጎ ሥራዎች ላይ በመሳተፍ ቀዳሚ ነው።
ምሕረት “በጎነት ቁሳዊ አልያም ገንዘብ ነክ ድጋፍ በመስጠት ብቻ አይወሰንም” ይላል። ሰዎች ገንዘብ ብቻ አይደለም የሚቸግራቸው። ለሰዎች ሊሰጡ የሚችሉ ከገንዘብ በላይ ውድ የኾኑ ብዙ ነገሮችም አሉ። ለሰዎች ጊዜን መስጠት ይቻላል። ለሁሉም ሰው በተፈጥሮ እኩል የተሰጠንን ደም በመለገስ አደጋ ውስጥ ያሉ ወገኖችን ገንዘብ የማይገዛው ሕይወት ማስቀጠልም ትልቅ በጎነት ነው። አካሉን ያጣ ወይም አቅሙ የደከመን ሰው ደግፎ መንገድ ማሻገርም በጎነት ነው። ከገጠር ወደ ከተማ ለጉዳይ ገብቶ መንገድ የጠፋውን ሰው እጁን ይዞ ጉዳዩን ወደሚፈጽምበት ቦታ ማመላከት እና ማገዝም በጎነት ነው። በዙሪያው ወዳጅ ዘመድ ላጣ ጆሮን በመስጠት ማዳመጥ እና ማወያየትም ትልቅ በጎነት ነው። ዕውቀት፣ ሃሳብ፣ ጊዜ ወዘተ ለሰዎች በበጎነት ልንሰጣቸው የሚችሉ ውድ ስጦታዎች ናቸው። “ቅን ልብ እና በጎ ሀሳብ ያለው ሰው ለሌሎች የሚሰጠው ነገር አያጣም” ይላል ወጣቱ።
በጎነት ለራስ ነው። ወጣት ምሕረትም ይህንኑ ይናገራል። የበጎ ሥራዎች ተሳትፎው ደስተኛ ሕይወትን እንዳተረፈለት ገልጿል። ለሰዎች በጎ መዋል ትልቅ የሕሊና እረፍት ይሰጣል ብሏል። በጎነት ዞሮ ይከፍላል። “ለሰዎች በጎ በማድረጌ ለኔም በርካታ ሰዎች በሕይወቴ ላይ በጎ አሻራዎችን አስቀምጠውልኛል” ብሏል ወጣቱ የበጎነቱን ክፍያ ሲናገር።
“ወጣቶች በበጎ ሥራዎች ላይ በመጠመድ፤ በጎ ካልኾኑ ነገሮች ደግሞ ፍፁም በመራቅ ነጋቸውን በበጎ መቅረጽ አለባቸው” ሲልም መልእክቱን አስተላልፏል። የነገዋ ሀገር በዛሬ ወጣቶች እጅ ነው የምትሠራው። ለሁሉም የምትመች ሀገር ለመገንባት በጎ የሚያስቡ፣ በጎም የሚሠሩ ወጣቶች ያስፈልጋሉ። ስለዚህ ወጣቶች የበጎ አድራጎት ማኅበራትን በመቀላቀል፣ አልያም አዳዲስ ማኅበራትን በመፍጠር በጎነትን ጠንካራ ባሕል አድርጎ ማዝለቅ አለባቸው ሲል መክሯል።
የዛሬው ቀን በጎነትን የምናስብበት መጭው አዲስ ዓመት ደግሞ በጎ ነገሮችን የምንሠራበት እንዲኾን ተመኘን!
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!