
ተማሪዎች የሌሎች አካላትን ፍላጎት በመሸከም አላስፈላጊ የህይዎት መስዋትነት መክፈል እንደሌለባቸው አስተያዬታቸውን የሰጡ የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተናገሩ፡፡
ትምህርት እና የተማረ የሰው ኃይል ለአንድ ሃገር ሁለንተናዊ እድገት ሚናቸው የጎላ ነው። ኢትዮጵያም በዘመናዊ ትምህርት አጀማመር ከምዕተ ዓመት በላይ የዘለለ ታሪክ አላት። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጅማሮም ከግማሽ ምዕተ ዓመት ያላነሰ ልምድ ባለቤት ናት። የአንድ ሃገር የተማረ የሰው ኃይል ማደግ ያለፈውን ለመመርመር፣ የአሁኑን ለመረዳት እና መጪውን ለመተንበይ የሚያስችል አቅም ይፈጥራል። የትምህርት ስርዓቱ በጥራት ችግር የተነሳ “ሰው መፍጠር አልቻለም” እየተባለ በሚብጠለጠልበት በዚህ ወቅት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሌላ ሳንካ ተጋርጦ ወቅታዊው የሃገሪቱ የፖለቲካ ውጥንቅጥ እያጠለሸው ይገኛል። በዚህም የተነሳ የተረጋጋ እና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን በአግባቡ እየከወኑ ያሉት የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን በጣት የሚቆጠሩ ከሆኑ ሰነባብቷል። በግጭት ምክንያት የተማሪዎች ህይዎት ማለፍ፣ የተማሪዎች እገታ፣ ‘ከአካባቢየ ወጣልኝ’ እና መሰል ችግሮች የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን ችግሮች ሆነዋል።
ችግሩ በአብዛኛዎቹ እንጂ በሁሉም አልተከሰተምና ሰላማቸውን አስጠብቀው ከሚገኙት መካከል ወደ ሰመራ ዩኒቨርሲቲ አመራን፤ ተማሪዎችን እና መምህራንንም አነጋገርን። በዩኒቨርስቲው 4ኛ ዓመት የህግ ተማሪ አህመድ ሙሃመድ “ሰመራ ዩኒቨርስቲ በ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ለአንድ ቀን እንኳን የመማር ማስተማሩ ስራ አልተቋረጠም” ብሎናል፡፡ እንደ ተማሪው ትዝብት ሰላም የሆነውም ሰላም የሚነሱ ችግሮች ሳይኖሩ ቀርተው ሳይሆን በተማሪዎች፣ በአካባቢው ማኅበረሰብ፣ በመምህራን እና በዩኒቨርስቲው የአስተዳደር ሰራተኞች ትጋት ነው። 12 ዓመታትን ለፍቶ የተማረ እና አነሰም በዛም በከፍተኛ ትምህርት ተቋም የመከታተል አቅም ያዳበረ ተማሪ መመረቅ ሲገባው መሞት የለበትም ያለው ተማሪ አህመድ ተማሪዎች የሌሎች አካላትን ፍላጎት በመሸከም አላስፈላጊ የህይዎት መስዋትነት መክፈል እንደሌለባቸውም ነው የመከረው።
“ብሄሩን ወይም ሃይማኖቱን ወክሎ የመጣ ተማሪ የለም፤” የመጣንበትን ዓላማ ብቻ አሳክተን እና ተመርቀን መመለስን ማሰብ እና ለዚያም ቀን ከሌት መስራት ይጠበቅብናል ነው ያለው ተማሪ አህመድ።
የ4ኛ ዓመት የምህንድስና ተማሪዋ ፅዮን እባቡ ደግሞ “የጋራ መኖሪያ እና መማሪያ ክፍሎቻችን የተለያዩ ሃይማኖቶችን እና ማንነቶችን በእኩልነት የተቀበሉ ቦታዎች ናቸው፤ በሰላም ተምሮ ለመመረቅ ሰው እና ተማሪ መሆናችን ብቻ በቂ ነው” ብላለች፡፡ ተማሪዎችን ለግጭት እየዳረጉ ያሉ ጉዳዮች ረብ የለሽ መሆናቸውንም ታዝባለች።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አደም ቦሪ (ዶክተር) እንደተናገሩት ደግሞ ሰመራ ዩኒቨርሲቲ አሁን ላለበት አንፃራዊ ሰላም አንድ እና ግልፅ የሆነ የመረጃ ልውውጥ ስርዓት መኖሩ እገዛ አድርጓል፡፡ የተማሪዎቻቸውን የሰላም ጥረትም አድንቀዋል። የአካባቢው ማኅበረሰብ ጠንካራ የሰላም እሴት፣ የመምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ቁርጠኝነት እና የተማሪዎቹ አርቆ አሳቢነት ለተገኘው ሰላም ምክንያቶች መሆናቸውንም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ:- ታዘብ አራጋው – ከሰመራ