“የኅሊና ትልቁ እርካታ በጎ ሥራ መሥራት ነው” የካለን ብናካፍል የሕጻናት፣ አረጋውያንና ሕሙማን መርጃ ማእከል

33

ባሕር ዳር: ጳጉሜ 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ)ኢትዮጵያውያን በሞት፣ በሕመም፣ በድንገተኛ አደጋ እና ሕይወትን ከሞት ለመታደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ የቆየ የመረዳዳት ግብረ ገባዊ እሴትን ያዳበሩ ሕዝቦች ናቸው።
ይሁን እንጂ መረዳዳቱ ዘላቂ እድገት በሚያመጡ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ባለመኾኑ ለችግሮች መወሳሰብ እና መግዘፍ ምክንያት እንደኾነ ስለግብረ ገብ የጻፉ ምሑር ጠና ደዎ(ዶ.ር) “ሰው ግብረገብና ሥነምግባር የዘመናችን ቁልፍ ጉዳዮች” በሚለው መጽሐፋቸው ይገልጻሉ።

ለአረጋውያን ጨምሮ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ችግር ላለባቸው ወገኖች በየትኛውም ሥፍራና ጊዜ ማንኛውንም ማኅበራዊ አገልግሎት መሥጠት እና መርዳት የዜጎች ግብረ ገባዊ ግዴታ ነው።

ሰብአዊነትን ተላብሰው ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውን አቅመ ደካሞችን በመደገፍ እና በመርዳት ግብረ ገባዊ ግዴታቸውን እየተወጡ ከሚገኙ በጎ ፈቃደኞች መካከል በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ‹‹ካለን ብናካፍል የሕጻናት፣ አረጋውያንና ሕሙማን መርጃ ማእከል›› አንዱ ነው።

ከማዕከሉ ስያሜ “ካለን” የሚለው የመጀመሪያ ቃል ፈጣሪ የሰው ልጅ ለተቸገረ እንዲረዳ ያስተላለፈውን ትዕዛዝ ለማመላከት እና “ከምናገኘው ለተቸገሩ ወገኖች እናካፍል” የሚል ሁለት ትርጉሞችን በመውሰድ የተመሠረተ ሥያሜ መኾኑን የማዕከሉ መሥራቾች ከኾኑት አንዱ እና አሁን ላይ ደግሞ የማዕከሉ ሥራ አሥኪያጅ ዳዊት አየነው ነግረውናል።

ሥራ አሥኪያጁ እንዳሉት መርጃ ማዕከሉ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በጎንደር ከተማ እና በጎንደር ሆስፒታል ውስጥ ችግር ውስጥ ለወደቁ ወገኖች አገልግሎት በመሥጠት ነበር ሥራውን የጀመረው።

ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ከጎንደር ከተማ አሥተዳደር ቦታ ወስዶ በመገንባት አረጋውያን፣ የአእምሮ ሕሙማንን፣ ደጋፊ የሌላቸው ሕጻናትን እና በጎንደር ሆስፒታል አስታማሚ የሌላቸው ወገኖችን ሕክምናቸውን እንዲጨርሱ ወደ ማዕከሉ በማስገባት እንክብካቤ እየተደረገላቸው እንደኾነም ገልጸውልናል።

ለትምህርት የደረሱ ልጆችን ደግሞ ትምህርት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው። አሁን ላይም 120 የሚኾኑ ተማሪዎችን እያገዙ እያስተማሩ እንደሚገኙ አንስተዋል። ካለባቸው ችግር ተላቅቀው ወደ ቤተሰቦቻቸው መመለስ የሚፈልጉ ወገኖችንም የማገናኘት ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በሦስት ሰዎች አገልግሎት መሥጠት የጀመረው ማእከል በዚሕ ወቅት 400 ለሚጠጉ ችግር ላይ የወደቁ ሰዎችን በማዕከሉ አገልግሎት እየተሠጠ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ማዕከሉ ከጎንደር ባለፈ በመላ ክልሉ ጭምር ለሚገኙ ወገኖች ነው አገልግሎት እየሠጠ የሚገኘው።

ማዕከሉ በሚሰጠው አገልግሎት በፌዴራል ደረጃም ዕውቅና እንዲያገኝ አድርጎታል፡፡

ከዚህ በፊት ከማኅበረሰቡ ፣ ከበጎ ፈቃደኞች ፣ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና ከውስን ተቋማት በሚደረግላቸው የአይነት፣ የጉልበት እና የገንዘብ ድጋፍ አገልግሎቱን ሲሰጡ መቆየታቸውን ሥራ አሥኪያጁ ነግረውናል። ይሁን እንጂ ማዕከሉ በቋሚ የገቢ ምንጭ ላይ የተመሠረተ ባለመኾኑ በኮሮና ወረርሽኝ እና በተለያዩ ጊዜያት በአካባቢው በተከሰቱ የጸጥታ ችግሮች የምግብ አቅርቦት ችግር እና የታመሙ ሰዎችን ሕክምና ለማድረስ ችግሮች እንደነበሩም ነው የነገሩን፡፡

በቀጣይ ወደ ማዕከሉ የሚገቡ አጋዥ እና ጧሪ ያጡ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በተጠናከረ መንገድ ለማገዝ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የማስፋፊያ ቦታ መረከባቸውን ገልጸዋል።

ማዕከሉን ለመገንባት ማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ላይ የሚሠሩ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የመንግሥት ተቋማት፣ በውጭና በውስጥ የሚገኙ ረጅ ድርጅቶች እና ባለሃብቶች ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ይህን ማድረግ ከተቻለ ማዕከሉ ባልደረሰባቸው ሌሎች አካባቢዎችም ተደራሽ በመኾን ችግር ውስጥ የወደቁ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ማገዝ እንደሚቻል ነው ያነሱት፡፡

በቦታው ተገኝቶ መደገፍ ለሚፈልግ ደግሞ በጎንደር ከተማ ቀበሌ 18 ሸዋ ዳቦ ወረድ ብሎ “ባምባ ሰፈር” በሚባለው ቦታ በመገኘት መጎብኘት እንደሚችሉም ነው የተገለጸው፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበጎነት ለሃገር!
Next articleአበበች ጎበና- የበጎነት አርአያ!