“ብዙ ደጋግ ሰዎች ባሉበት ሀገር ብዙ ችግረኛ ሰዎች መኖር የለባቸውም” ሽኩር አህመድ የምርኩዝ በጎ አድራጎት ማኅበር ምክትል ሥራ አስፈጻሚ

67

ባሕር ዳር: ጳጉሜን 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በጎነት በጎ ከማሰብ ይጀምራል፡፡ በበጎ ሃሳብ ለበጎ ተግባር የተሰባሰቡ የቅን ልቦች በጎ አሻራ ደግሞ ለትውልድ ይተርፋል፡፡ በየአካባቢው በርካታ ድጋፍ ለሚሹ ሰዎች የመፍትሔ አካል፣የደስታቸውም ምንጭ የኾኑ የበጎ አድራጎት ማኅበራትን መጥቀስ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ እርግጥ ነው ሰዎችን በበጎነት የማገዝ ሂደት መዳረሻው የአእምሮ እርካታ ነው፡፡ በጎነት ለራስ ነው እንዲሉ በጎነት ክፍያው ደስታ ነውና፡፡

አቶ ሽኩር አህመድ ምርኩዝ የልማት ፣የትምህርትና የማሕበራዊ ድጋፍ በጎ አድራጎት ማኅበር ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡ማኅበሩ መቀመጫውን ባሕር ዳር ከተማ ላይ አድርጎ ከቅን ልቦች በሚያገኘው ድጋፍ በቅንነትና በበጎነት በተሰባሰቡ የማኅበሩ አባላት ተሳትፎና ቅንጅት የተቸገሩትን ይደግፋል ይላሉ፡፡

ማኅበሩ በቋሚነትና በጊዜያዊ መልኩ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ድጋፍ ያደርጋል የሚሉት አቶ ሽኩር በቋሚነት ለ106 ቤተሰቦች ከ700 እስከ 1500 ብር ወርሐዊ የገንዘብ ድጋፍ ይደረግላቸዋል ብለዋል፡፡ ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮም በዓላትንና ልዩ ልዩ ኹነቶችን መሰረት አድርጎ የተቸገሩትን ይደግፋል ነው ያሉት፡፡ በቀጣዩ አዲስ ዓመትም የተለመደ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት፡፡ እናም ለ1000 የችግረኛ ቤተሰብ ተማሪዎች የደብተርና እስክርቢቶ ድጋፍ ለመስጠት እየተዘጋጁ ስለመኾኑ ተናግረዋል፡፡

በቋሚነት የገንዘብ ድጋፋ የሚደረግላቸውን ችግረኛ የምርኩዝ ቤተሰቦችም ከ106 ወደ 150 ከፍ ለማድረግ ዕቅድ ተይዟል ነው ያሉት፡፡ የተቸገረን እንደመርዳት የሚያስደስት የለም የሚሉት ምክትል ሥራ አስፈጻሚው ሽኩር አህመድ የማኅበሩ መመስረት ዓላማና ግብም ለሰዎች ችግር የመፍትሔ አካልና የደስታቸው ምክንያት መኾን ነው ብለዋል፡፡

ምክትል ሥራ አስፈጻሚው አንድ መልእክት አላቸው “ብዙ ደጋግ ሰዎች ባለሉበት ሀገር ብዙ ችግረኛ ሰዎች መኖር የለባቸውም” በጎ ዓለም ለመፍጠር በጎ ሰዎችን ማብዛት ይገባል፣ለዚህ ደግሞ በጎ አሻራቸውን ለማስቀመጥ፣ በየአካባቢው የሚቸገሩ ፣ከችግራቸው ብዛትም የሚከፉ ወገኖቻችን እንዳይኖሩ የሚጥሩ የበጎ አድራጎት ማኅበራትን መደገፍ ማገዝ፣ማበርታት ይገባል ነው የሚሉት፡፡ እንዲህ አይነት የበጎ አድራጎት ማኅበራት ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች መድረስ ሀገርን መደገፍ፣መንግሥትንም ማገዝ መኾኑ ሁሉም ልብ ሊለው ይገባል ይላሉ፡፡

ምርኩዝ አቅሙ አድጎ የድጋፍ እጁ ለብዙዎች እንዲደርስ ቅን ልቦና ያላቸው ሰዎች ፣ ባላሃብቶች ፣የቢዝነስ ተቋማትና መንግሥት የምርኩዝን የበጎ አድራጎት ዓላማ ተረድተው ድጋፋቸውን እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡ በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጭ ለምርኩዝ ብርታት የኾኑ አካላትም ላደረጉትና ወደፊትም አብረው ስለሚጓዙ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

አቶ ሽኩር እንደሚሉት በአንድ በኩል ብዙ ችግረኞች ያሉበት፣በሌላ በኩል ደግሞ ብዙ ደጋጎች ያሉበት ሀገር መፈጠሩ ፣ወይም ደግሞ በአንድ በኩል የእለት ጉርሱን ያጣ፣ በሌላ በኩል የሃብት ማማ ላይ የወጣ የተዛነፈ ዓለም መፈጠር በጎነት ላይ በሥፋት የአለመሠራቱ ማሳያ ነው ይላሉ፡፡ የተቸገሩትን እና ደጋፊ የሌላቸውን በበጎ ፈቃድ ለማገዝ ቀንና ኹኔታን መጠበቅ ባያስፈልግም ኹነቶችን ፤በዓላትን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም አስታዋሽ ቅስቀሳዎችን በማድረግ፣የበጎነት ባሕልን ማጎልበት የሚደገፍ ተግባር ነው ብለዋል፡፡

በተለይም አሁን ላይ የጳጉሜ 4 ቀንን” የበጎነት ቀን” ተብሎ መሰየሙም በጊዜ ማጣት፣በመዘናጋትና በሌላም ምክንያት በጎ ከማድረግ የተዘናጉ አካላትን ማስታወሻ ነውና መልካም ተግባር ነው ብለዋል፡፡ ምንም እንኳን በጎነት ለምርኩዝ የበጎ አድራጎት ማኅበር የአዘቦት ተግባሩ ቢኾንም ቀኑ የበጎነት ቀን በመኾን በጎ ተግባራት የሚስፋፉበት፣ለብዙዎችም የምንደርስበት እድል እንዲፈጠር ይሰራል ነው ያሉት፡፡ እንደ ቀደመ አባቶቻችን መደጋገፍና መረዳዳት ባሕላችን እና ቀለማችን እንዲኾን አሁን ላይ እየፈተነን ካለው ግዴለሽነት፣ግለኝነት፣የሌላውን ችግርና ሕመም የአለመረዳት ችግር ለመቅረፍ የብዙኃን መገናኛ ተቋማት በርትተው ቢሰሩ መልካም ነው ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡-ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“እንደዚህ ነው ካህን እንደዚህ ነው አባት ስለ ፍቅር ሞቶ ታላቅ ሀገር ማጽናት”
Next articleበጎነት ለሃገር!