
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሞት ፊት ኾኖ ሀገርን ማፍቀር እንደምን ያለ ፍቅር ነው? በሞት አውታር ተይዞ ስለ ሀገር መኖር እንደምን ያለ መታደል ነው? በገዳዮች ፊት ኾኖ ስለ እውነት መጽናት እንደምን ያለ ጽናት ነው? በሞት መንጋጋ ተከቦ ሞትን መናቅ እንደምን ያለ መሰጠት ነው? በጨካኝ ወታደሮች ሰይፍ መካከል ኾነው አምላካቸውን ማሰብ፣ ስለ ሃይማኖታቸውም መናገር እንደ ምን ያለ እምነት ነው? በሀሰተኞች ችሎት፣ በሀሰተኛ ፈራጆች ፊት ቆሞ ስለ እውነት መመስከር፣ ስለ እውነትም መኖር እንደምን ያለ እውነት ነው?
ብጹዕ ናቸው ጸጋ የበዛላቸው፣ ካህን ናቸው የአምላክ በረከት የማይለያቸው፣ ኩሩ አርበኛ ናቸው ጠላቶቻቸውን በመስቀል የሚጥሉ፣ በቀኝና በግራ እልፍ የሚያስገብሩ፡፡ በሀሰተኞች አደባባይ ተገኝተው ሀሰተኞቹን አስጨነቋቸው፣ ለሞት ተዘጋጅተው ገዳዮቹን አስደነገጧቸው፣ ጦር በታጠቁት፣ እሳት የሚተፋ አፈሙዝ በጨበጡት ጨካኞች ፊት ቆመው አርበደበዷቸው፡፡ እርሳቸው እንደጠላቶቻቸው ሁሉ እሳት የሚተፋ ጦር አልሰበቁም፣ አንገት የሚቀላ ጎራዴ አላሰሉም፣ ደረት የሚወጋ ጦር አላሾሉም፣ እውነት፣ ነጻነትና ሃይማኖት ብቻ ይዘው ድል መቷቸው፡፡ በሞታቸው ገደሏቸው፣ በእውነታቸው ሀሰተኞቹን በጭንቅ አውታር ያዟቸው፡፡
ስለ ፍቅሯ ሞተዋልና ምድሯ ጴጥሮስ ጴጥሮስ ትላለች፣ ስለ ክብሯ መስዋእት ኾነዋልና ስማቸውን እየደጋገመች ትጠራለች፣ ጴጥሮስ ሰማእት እያለች ታከብራለች፣ ቃል ኪዳናቸውን ትጠብቃለች፣ ለልጆቿ ታስተምራለች፣ በማይጠፋ ቀለም፣ በማያረጅ ብራና ቀርጻ አስቀምጣለች፣ ዓመታት አልፈው ዓመታት ሲከተሉ ትዘክራቸዋለች፡፡
ኢትዮጵያን አብዝተው ወደዷት፣ ታላቅነቷን በጠላቶቿ ፊት መሰከሩላት፣ ነጻነቷን በደማቸው አጸኑላት፣ በገዳዮቻቸው ፊት እውነቷን ተናገሩላት፣ በሞት ፊት ኾነው ትውልድ ሁሉ ይጠብቃት ዘንድ ቃል ኪዳን አኖሩላት፣ ዘመን የማይሽረው፣ ትውልድ የማይጥለው፣ ሀሰት የማይከልለው የእውነት ቃል ተውላት፡፡ እርሷን የሚክደውን ካዱት፣ እርሷን የሚወደውን ወደዱት፣ በቀና ልባቸው፣ አምላክ በመረጠው ብጽዕናቸው መረቁት፡፡ ሃይማኖታቸውን በርትተው ጠበቋት፣ ትዕዛዛቷን አከበሩላት፣ አክብረውም አስከበሩላት፡፡
ወሰን እና ልክ የሌለው የሀገር ፍቅራቸው ሞትን አስንቋቸዋል፣ የጥይት አረርን አስረስቷቸዋል፡፡ መከራና ስቃይን አስችሏቸዋል፡፡ በሀገራቸው እና በሃይማኖታቸው የመጣባቸውን ጠላት ፊት ለፊት ታገሉት፣ ባሩድ የሚተፋ ጠመንጃ ይዞ እያስፈራራቸው ናቁት፣ መሳደድም ቢኾን፣ መሰቃየትም ቢኾን፣ መጠማትም ቢኾን፣ መራብም ቢኾን፣ መታሰርና መገረፍም ቢኾን፣ ሞትም ቢኾን ሃይማኖታቸውን፣ ሀገራቸውን እና ነጻነታቸውን ከመጠበቅ እንደማያቆማቸው ነገሩት፡፡
ጠላቶቻቸው ገድለው ነጻነታቸውን፣ ሃይማኖታቸውን እና ሀገራቸውን አሳጣናቸው ሲሉ እርሳቸው ግን በሞታቸው አሸነፏቸው፣ በቃል ኪዳናቸው ድል መቷቸው፣ እረኛውን ገድለን በጎችን በተናቸው ሲሉ እርሳቸው ግን በሞታቸው በጎቻቸውን ሰበሰቧቸው፣ በቃል ኪዳናቸው አንድ አደረጓቸው፣ ከዳር እስከ ዳር አሰባሰቧቸው፣ በቃል ኪዳን፣ በግዝት አስረው ለሀገራቸው ነጻነት አስነሷቸው፡፡ እስከ ሞት ድረስ በታመነው የሀገር ፍቅራቸው ነጻነትን አምጥተዋል፣ ሕዝብን አንድ አድርገዋል፡፡ አርበኞችን በእልህና በወኔ አስነስተዋል፡፡
“ ለአረበኞች መሞትን ማን አስተማራቸው
አቡነ ጴጥሮስ ነው ባርኮ የሰጣቸው” የተባለላቸውም ለዚያ ነው፡፡ አምላክ የመረጣቸው ብጹዕ ናቸው፡፡ ትውልድ ሁሉ የሚወዳቸው፣ የሚመካባቸው ሰማዕት ናቸው፡፡ ረቂቁን የሚያነጥሩ፣ ምስጢር የሚያሜሰጥሩ ሊቅ ናቸው፡፡ ከበጎቻቸው በፊት የሚቀድሙ፣ ስለ ፍቅር ለመስዋእት የቀረቡ ደግና ታማኝ እረኛም ናቸው ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ፡፡
ዓድዋ ላይ በኀያል ክንድ የደቀቀችው፣ ከሮም ተጉዛ በኢትዮጵያ ተራራዎች ለኢትዮጵያ የሰገደችው፣ ፎክራ መጥታ አልቅሳ የተመለሰችው፣ ንቃ መጥታ የተዋረደችው፣ ክብር አዋርዳለሁ፣ ነጻነት እገፋለሁ፣ ሀገር አሳጣለሁ ስትል በብርቱ ጀግኖች የተዋረደችው ኢጣልያ ከአርባ ዓመታት በኋላ ለበቀል መጥታ ነበር፡፡ በአምባላጌ፣ በመቀሌና በዓድዋ ላይ ደማቸው የፈሰሰባትን፣ አጥንታቸው የተከሰከሰባትን የልጆቿን ደም ልትመልስላቸው፣ የጣለችውን ክብሯን ልታነሳው፣ ውርደቷን ልትክሰው ዳግም ከሮም ተነስታ ወደ ኢትዮጵያ መጣች፡፡
በዘመኑ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከአባቶቻቸው የወረሱትን ኀላፊነት ተቀብለው በዙፋኑ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ መቼም በዚያ አስፈሪ ዙፋን ላይ የሚቀመጥ አስፈሪ ንጉሥ ሁሉ ሀገሩን ይጠብቃት፣ ከጥንት ጀምሮ የቆየውን ነጻነቷን ያስከብርላት ግድ ነው፡፡ በነጻነታቸው የሚመጣን ጠላት አይታገሱም፣ ምድሯ ሰው አጥታ ምድረ በዳ እስክትኾን ድረስ ነጻነታቸውን አሳልፈው አይሰጡም፡፡
ንጉሡ ኃይለ ሥላሴ የአባቶቻቸውን ገድል ያውቃሉ፡፡ የሀገራቸውንም ኀያልነት ጠንቅቀው ይረዳሉ፡፡ በአባቶቻቸው ዘመን መጥቶ ድል የተመታው ጠላት በእርሳቸው ዘመን ሲመጣ ከጠብ ፍቅር ይሻላል አሉ፡፡
ጠላቶቻቸው ግን የፍቅር ስሞታውን ወደ ጎን ገፉት፡፡ ያን ጊዜ የሀገራቸውን ጀግኖች ጠሩ፡፡
ጀግኖቹም እንደ ከንፈር ንክሻ፣ እንደ ዓይን ጥቅሻ በፍጥነት ተሰባሰቡ፡፡ በእልህና በወኔም ዘመቱ፡፡ ንጉሡ ኃይለ ሥላሴም በእልህና በወኔ ዘመቱ፡፡ እርሳቸው ወደ ማይጨው ሲዘምቱ ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስም አብረው ዘማች ነበሩ፡፡ ብጹዕነታቸው የሀገራቸውን ጀግኖች በጸሎት እያበረቱ፣ አምላካቸው ሀገራቸውን እንዲጠብቅላቸው እየተማጸኑ ነበር ወደ ማይጨው ያቀኑት፡፡ ጠላት አብያተክርስቲያናትን እያቃጠለ፣ ካህናትን እየገደለ፣ ምዕመናንን በመርዝ እያሰቃዬ ነበርና እረኛው እኔም ለበጎቼና ለሀገሬ እዘምታለሁ ብለው ዘመቱ፡፡
ጦርነቱ የከፋ መስዋእትነትን የሚጠይቅ ረጅም ጊዜም የሚወስድ ነበር፡፡ በአንድ ጀንበር ድል የሚገኝበትም አልነበረም፡፡ የኢትዮጵያ ጀግኖች በዱር በገደሉ ከጠላት ጋር መፋለማቸውን ቀጠሉ፡፡ ጦርነቱ በዱር በገደሉ ቀጠለ፡፡ ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስም ሀገራቸውን ላለማስደፈር የሚዋደቁትን ጀግኖች ያበረታቷቸዋል፣ ያለ ድካም ይጸልዩላቸዋል፡፡
ጦርነት ቀጠለ፡፡ ጳውሎስ ኞኞ የኢትዮጵያና የኢጣልያ ጦርነት በሚለው መጽሐፋቸው ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ ከማይጨው ከተመለሱ በኃላ ሚያዚያ 24 ቀን ደብረ ሊባኖስ ገቡ፡፡ ከዚያም ኾነው የሰላሌን አርበኞች በስብከት ያነቃቁ ጀመር፡፡ በዚህም ለኢጣልያ የገቡና በኢጣልያ አገዛዝ ያመኑ የኢትዮጵያ ቀሳውስት አቡነ ጴጥሮስ ለኢጣልያ እንዲገቡና በኢጣልያ ላይ የሚነዙትን አጉል ስብከት እንዲተዉ በደብዳቤም በቃልም ይመክሯቸው ጀመር፡፡ አቡነ ጴጥሮስ ግን ማንኛውንም ልመና አልተቀበሉትም ብለዋል፡፡
የእሳቸው ሃሳብና ተግባር እውነት ነበር እንጂ አጉል አልነበረምና እንዲያስተዋቸው ለሚጠይቃቸው ሁሉ ጀሮ አልሰጡትም፡፡ የኢትዮጵያ ጀግኖች በየቀኑ የዙፋን መቀመጫዋን አዲስ አበባን ለማስለቀቅ ይዋጋሉ፡፡ የኢጣልያ ሠራዊትም ይሸበራል፡፡ ጳውሎስ ኞኞ ፓትሪክ ሮበርትስንን ጠቅሰው ሲጽፉ “ ኢትዮጵያውያኖች የሚያስገርምና ከባድ ውጊያም አደረጉ፡፡ ወደ አዲስ አበባ ከተማ እየተጠጉ ሲሄዱም ጥቅጥቅ ካለው ደን ውስጥ ሲገቡ የኢጣልያ ተከላካይ ወታደሮች ጉዳት አደረሱባቸው፡፡ ሁለት ቀን ሙሉ በጀግንነት ተዋግተው ኢትዮጵያውያኖቹ ይዘውት የነበረውን ቦታ ትተው ሲመለሱ ጳጳሱ አቡነ ጴጥሮስ ተማረኩ፡፡ አቡነ ጴጥሮስ ከተማዋ ድረስ ከአርበኞቹ ጋር አብረው የመጡ ናቸው፡፡ የተያዙትም በጦርነቱ ውስጥ ነው” ብሏል በማለት ጽፈዋል፡፡
ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን በተሰኘው መጽሐፍ ደግሞ “ ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ አርበኞች ከአዲስ አበባ ሲመለሱ እሳቸው ግን የአዲስ አበባ ከተማን ትተው ለመሄድ አልፈቀዱም፡፡ በመኾኑም ብችል ጠላት በኢትዮጵያውያን ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍ የሚመለከተውን ሕዝብ በማትጋት በጠላት ላይ እንዲነሳ አደርጋለሁ ካልኾነ ደግሞ እዚሁ እሞታለሁ ብለው ከአርበኞች ተነጥለው በአዲስ አበባ ቀሩ፡፡ ይሁን እንጂ ጠላት በመላ ከተማዋ ባሰማራቸው በርካታ ባንዳዎች ምክንያት ብፁዕነታቸው እንዳሰቡት ሊንቀሳቀሱ አልቻሉም፡፡ በዚሁ በከተማም ተሰውሬ መኖር አልፈልግም ወደገጠርም ፊቴን አልመልስም በማለት ለኢጣልያ እንደራሴ እጃቸውን ሰጡ፡፡ የኢጣልያ እንደራሴም ወዲያው ለግራዚያኒ አሳልፈው ሰጧቸው ” ብለዋል፡፡ የኢጣልያ እንደራሴ የነበሩትም ኢትዮጵያዊ ሰው ናቸው፡፡
ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ በፋሽሽቶች እጅ በገቡ ጊዜ ሞት ተፈረደባቸው፡፡ ብጹዕ ኾነው ሳለ እንደ በደለኛ ሞት ተፈረደባቸው፣ ሃይማኖት ጠባቂ፣ የሀገር ፍቅር አዋቂ ኾነው ሳለ እንደ ወንበዴ ሕዝብ በተሰበሰበበት፣ ታናሽና ታላቁ ባለበት ለመቀጣጫ ይገደሉ ተባሉ፡፡ ሀገሬን አትንኩ፣ ሃይማኖቴን አትዳፈሩ ባሉ እንደ ሀጥያተኛ ተቆጠሩ፡፡ ጳውሎስ ኞኞ የኮሪየር ዴላ ሤራ ጋዜጠኛ የነበረውን ፓጃሊን ጠቅሰው ሲጽፉ “ በጳጳሱ ላይ የተቋቋመው ችሎት ሕዝብ በተሰበሰበበት በአደባባይ እንዲገደሉ ፈረደ፡፡ ይህ ሲሰማ በከተማው ሕዝብ ዘንድ ሽብር ፈጠረ፡፡ ጉዳዮም በጋዜጣ እንዳይወጣ ፋሽሽቶች ታላቅ ቁጥጥር አደረጉ” ብለዋል፡፡
ፍርዱ ተፈረደ፡፡ ጳጳሱ ከሞት ደጅ፣ ከገዳዮች ፊት ቆሙ፡፡ ከሳሾቻቸውና ፈራጆቻቸው ጥያቄ አቀረቡላቸው፡፡ ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን በተሰኘው መጽሐፍ “ ካህናቱም ኾኑ የቤተክህነት ባለስልጣኖች ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስም የኢጣልያን መንግሥት ገዢነት አምነው አሜን ብለው ሲቀበሉ እርስዎ ለምን አመፁ? ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ ኾኑ? ሲል ጠየቃቸው፡፡ አቡነ ጴጥሮስም መለሱ፡፡ አቡነ ቄርሎስ ግብጻዊ ናቸው፡፡ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም፡፡ እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ ኀላፊነትም ያለብኝ የቤተክርስቲያን አባት ነኝ፡፡ ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ፡፡
ከዚህ በቀር ለእናንተ ችሎት የማይቀርበው ነገር የለኝም፡፡ ለፈጣሪዬ ብቻ የምናገረውን እናገራለሁ” ማለታቸው ተጽፏል፡፡ በንጹሕ ልባቸው የጸናች እውነታቸውን ለአምላካቸው ነገሩት፡፡
አቡነ ጴጥሮስ ወደ መግደያው ሥፍራ ተወሰዱ፡፡ በዚያም ሥፍራ እጅግ የከበረውን፣ ትውልድን ከትውልድ ጋር የሚያስተሳስረውን፣ የሀገር ፍቅርን የሚያጸናውን፣ ዘመናትን አልፎ የሚሰማውን ቃል ከሚጣፍጥ ልሳናቸው ሰጡ፡፡ ለትውልድም እንዳይጠፋ አድርገው በልብ መዝገብ ላይ አስቀመጡ፡፡ “ ከሚገደሉበት ሥፍራ ሲደርሱ አራቱን ማዕዘን በመስቀላቸው ባረኩ፡፡ በሕዝቡም ፊት ቆመው እንዲህ አሉ፡፡ ፋሽሽቶች ያገራችንን አርበኞች ሽፍታ ቢሏቸው እውነት አይምሰላችሁ፡፡
ሽፍታ ማለት ያለ ሀገሩ መጥቶ የሰውን ሀገር የሚወር ይህ በመካከላችሁ የቆመ አረመኔው የኢጣልያ ፋሽሽት ነው፡፡ አረማዊ የኾነው የፋሽሽት መንግሥት ቤተ ክርስቲያንን ለማቃጠል ሕዝበ ክርስቲያንን ለመግደል፣ ሃይማኖትን ለማጥፋት፣ ታሪካችንን ለማበላሸት የመጣ ነው፡፡ በጎ ለመሥራት እውነትን ለመፍረድ ለመስጠት ስላልመጣ ለዚህ ለግፈኛ አትገዙ፡፡ ስለ ውድ ሀገራችሁ፣ ስለ ቀናች ሃይማኖታችሁ ተከላከሉ፡፡ ነጻነታችሁ ከሚረክስ ሞታችሁ ስማችሁ ሲቀደስ ታላቅ ዋጋ ያለው ክብር ታገኛላችሁ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዚህ ለጠላት እንዳይገዛ አውግዣለሁ፡፡ የኢትዮጵያ መሬት ጠላትን ብትቀበል የተረገመች ትሁን፡፡ በፈጣሪዬ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተገዘተች ትሁን” አሉ፡፡
አቡነ ጴጥሮስን ገድለው ክብር ማግኘት የሚሹ ገዳዮች ለመግደል አኮበኮቡ፡፡ ከአቡነ ጴጥሮስ ሃያ እርምጃ ያክል ርቀው በርከክ አሉ፡፡ በአስተኳሹ ትዕዛዝም ተኮሱ፡፡ አቡነ ጴጥሮስ ጀርባቸው ተበሳሳና ከመሬት ላይ ወደቁ፡፡ አልሞቱም ነበርና በድጋሜ በሦስት ጥይት ራሳቸውን ተመትተው ተገደሉ፡፡ ታላቁ አባት ታማኙ እረኛ በጽኑ እምነት አለፉ፡፡ የእርሳቸውን ሞት የሰሙ ሁሉ አባታችን እያሉ አለቀሱ፡፡ አርበኞችም የታላቁ አባት መስዋዕትነት ወኔ እየኾናቸው ለነጻነት ለመሞት ቆረጡ፡፡
“እንደዚህ ነው ካህን እንደዚህ ነው አባት ስለ ፍቅር ሞቶ ታላቅ ሀገር ማጽናት” ስለ ሀገር ፍቅር ሞተው ታላቅ ሀገር አጸኑ፡፡ ትውልድን በቃላቸው አስተሳሰሩ፡፡ ስለ ሀገር ክብር መሞት፣ ስለ ሠንደቅ ፍቅር መስዋት ከከበረም የከበረ፣ ከተወደደም የተወደደ ክብር መኾኑን አሳዩ፡፡ በመስዋዕትነታቸው የደም ማሕተም ሀገራቸውን ነጻ አወጡ፡፡ በታላቅ ሀገር የተገኙ ታላቅ ሀገርም በመስዋእትነት፣ በጽኑ አምነት የሰጡ አባት ኾይ እውነትዎ ሁሉ በትውልዱ ልብ ይጻፍ፤ የኑዛዜ ቃልዎ በልብ ላይ ይረፍ፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!