ሕዝቡ የተጀመረው ሰላም ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲሸጋገር የራሱን አስተዋጽዖ እንዲያደርግ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ጥሪ አቀረቡ፡፡

62

ባሕር ዳር: ጳጉሜን 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በክልሉ ወቅታዊ ጉዳይ እና በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ሰላሙ ዘላቂ እንዲኾን፣ የልማት ሥራዎች እንዲጀመሩ፣ የመልካም አሥተዳደሩ ሥራ በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲሄድ መንግሥት እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የመጀመሪያው ተግባር ከክልል ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ ያለውን የመንግሥት መዋቅር መልሶ የማደራጀት ሥራ ጀምረናል ብለዋል፡፡ የመንግሥት መዋቅሩን መልሶ የማደራጀት ሥራ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ እየሠሩ መኾናቸውንም አመላክተዋል፡፡

የሕዝብን መሰረታዊ፣ የልማት ፣ የዴሞክራሲና በተደጋጋሚ እንዲፈቱለት ሲጠይቃቸው የቆዩ ጥያቄዎችን ለመፍታት የፖለቲካ መሪዎችን መልሶ ማዋቀር ማስፈለጉንም ገልጸዋል፡፡ ጥያቄዎችን መፍታት የሚችሉ ጠንካራ መሪዎችን ለማደራጀት ጥረት እያደረጉ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ አዲስ የሚዋቀረው መሪ የሕዝብን መብትና ጥቅም ለማስከበር እንዲችልና ተልእኮን በብቃት እንዲወጣ የሚያስችል ሥራ እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡

መልሶ የማደራጀቱ ሥራ እስከ መስከረም መጨረሻ ድረስ እንዲጠናቀቅና የመንግሥት መዋቅር በተጠናከረ ሁኔታ ወደ መደበኛ ሥራው እንዲገባ ርብርብ እየተደረገ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ የክልሉን የጸጥታ መዋቅር እንደገና ለማደራጀት ጥረት እያደረጉ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ በክልል ደረጃ የፖሊስ፣ የሚሊሻና ሌሎች የጸጥታ አስከባሪ ተቋማትን እንደገና ለማደራጀት ጥረት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡ የጸጥታ መዋቅሩን እንደገና የማደራጀት ተግባር እስከ ቀበሌ ድረስ ይቀጥላልም ብለዋል፡፡

የጸጥታ ተቋማት የክልሉን ሰላምና ደኅንነት በማስከበርና የሕግ የበላይነት እንዲከበር ለማድረግ አይነተኛ ሚና እንዲጫወቱ ለማድረግ የሚያስችል የማደራጀት ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡ የመንግሥት አሥተዳደር እና የጸጥታ ተቋማት ተቀናጅተው ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ እየሠራን ነውም ብለዋል፡፡ የተቋረጠውን መደበኛ አገልግሎት እንደገና ማስጀመር እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ የግብርና፣ የኢንዱስትሪ ዘርፍ፣ የማኅበራዊ ልማት እና ሌሎች ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ዕቅዳቸውን አጠናቀው ወደ ሥራ እየገቡ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ የማኅበረሰብን ጤና የሚጎዱ በሽታዎችን የመከላከል ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ የትምህርት ተቋማት እንዲከፈቱና መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራቸውን እንዲቀጥሉ እየተሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡ በግብርናው ዘርፍም በትኩረት እየሠሩ መኾናቸውን ነው የገለጹት፡፡ በግጭት ምክንያት የተቋረጡ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችም ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል ነው ያሉት፡፡

በክልሉ በሁሉም አካባቢ መደበኛ የመንግሥት አገልግሎት እንዲጀምር፣ የዜጎችን እንቅስቃሴዎች የሚገድቡ አካሄዶችን የማስተካከል ሥራ እየሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ሕዝቡ የተጀመረው ሰላም ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲሸጋገር የራሱን አስተዋጽዖ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ክልሉ አሁን ላይ በጣም በተሻለ የጸጥታ ሁኔታና ወደ ነበረበት ሰላም እየተመለሰ መኾኑን ለሕዝባችን ማብሰር እወዳለሁ” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next article“እንደዚህ ነው ካህን እንደዚህ ነው አባት ስለ ፍቅር ሞቶ ታላቅ ሀገር ማጽናት”