የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ መኖሪያቸው ለመመለስ የሚያስችል እርቀ ሰላም እየተካሄደ ነው፡፡

428

ባሕር ዳር ጥር 7/2012ዓ.ም (አብመድ) በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቀደም ሲል በተፈጠሩት ግጭቶች የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ እና በአካባቢው ዘላቂ ሠላም ለማስፈን እርቀ ሰላም እየተካሄደ ነው፡፡

በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ ማንቡክ ላይ በተካሄደው የዕርቀ ሠላም ኮንፈረንስ ላይ እንደተገለጸው ባለፈው ሚያዚያ 2011 ዓ.ም የተፈጠረው ግጭት የሕይዎት መጥፋት፣ የንብረት መውደም እና መፈናቀል አስከትሏል፡፡ ችግሮች እንዳይደገሙና ዘላቂ ሰላም እንዲኖር ለማድረግ በማሰብም በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ በተለያዩ ቀጣናዎች የእርቀ ሠላም ኮንፈረንሶች እየተካሄዱ ነው፡፡

የእርቀ ሰላም ኮንፈረንሱ በግጭት ምክንያት ከኖሩበት፣ ሃብት ካፈሩበትና ካደጉበት ቦታ ተፈናቅለው በየአካባቢው ተበታትነው ለችግር የተዳረጉ በርካታ የአማራ ተወላጆች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ትልቅ እገዛ እንደሚደርግ ታምኗል፡፡ ከጃዊ እና አካባቢው ተፈናቅለው ለችግር የተዳረጉ የቤኔሻንጉል ጉምዝ ክልል ተወላጆችን መልሶ ለማቋቋም የሚኖረው ፋይዳም ከፍተኛ ነው ተብሏል በውይይቱ፡፡

በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚፈጠሩ ግጭቶችን በዘላቂነት ለማስቆም የአማራ እና የቤኔሻንጉል ክልል መንግስታት እና ሕዝቦች በጋራ መስራት እንዳለባቸው በእርቀ ሠላም ኮንፈረንሱ ተጠይቋል፡፡ በሕዝብ መካከል ገብተው ግጭቶችን በመፍጠር የሚጠቀሙ ደላሎች መኖራቸውንና መንግስት ተጨባጭ እርምጃ አለመውሰዱ ችግሩን እንዳባባሰም ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡ በተፈጠረው ችግር ምክንያትም በመተከል ዞን ሊለማ የሚችል ሰፊ መሬት አለመልማቱን ጠቁመዋል፡፡ ይህም ብዙዎቹን ለረሃብ የሚዳርግ በመሆኑ በአካባቢው ዘላቂ ሠላምን ማስፈን ጊዜ ሊሰጠው እንደማይገባ ነው ያሳሰቡት፡፡

አብመድ ያነጋገራቸው የሁለቱም ክልል የሥራ ኃላፊዎች ባለፈው በተከሰተው ግጭት ተሳታፊ ነበሩ የተባሉ መሪዎችን ጨምሮ እርምጃ መወሰዱን እና የአካባቢውን ሠላም በማስጠበቅ የተሻለ መስራት የሚችሉ መሪዎች መተካታቸውን ተናግረዋል፡፡ የተፈናቀሉ ዜጎችንም ወደ ቀያቸው ለመመለስ እና ለማቋቋም የሁለቱም ክልሎች በጋራ እየሰሩ መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች የመጠለያ ግንባታው መጠናቀቁን የተናገሩት የሥራ ኃላፊዎቹ አሁንም በርካታ ዜጎች ተፈናቅለው በየቦታው ተበታትነው ለችግር የተጋለጡ በመሆኑ ድጋፍ ተደርጎላቸው መቋቋም የሚችሉበት ሁኔታ ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ጉዳይ መሆኑን ታዝበናል ነው ያሉት፡፡ ኅብረተሰቡም በሕዝቦች መካከል ግጭቶችን በመፍጠር ለሚያተርፉ አካላት መጠቀሚያ ከመሆን እንዲቆጠብ እና ሁኔታዎችን በአስተውሎት ሊያይ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አብዮት ከፋለ

Previous article“በጎንደር እና አካባቢው የጥምቀት በዓል ላይ ከ2 ሚሊዮን በላይ ታዳሚዎች ይገኛሉ፡፡” ባህልና ቱሪዝም ቢሮ
Next article“በብሄሩ ወይም በሃይማኖቱ ውክልና ተሰጥቶት የመጣ ተማሪ የለም።” የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች