
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ በክልሉ ወቅታዊ ጉዳይ እና በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫቸውም የአማራ ክልል ባለፉት ሳምንታት በከፍተኛ የጸታ ችግር ውስጥ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በክልሉ የተከሰተው ቀውስ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ማስከተሉንም ገልጸዋል፤ በመላ ሕዝቡ አስተዋይነት እና ተሳትፎ፣ በጸጥታ መዋቅሩ ግዳጅን የመወጣት ብቃትና በየደረጃው በሚገኙ መሪዎች ትብብር ቀውሱ አደጋ ወደማይኾንበት ደረጃ ደርሷል ብለዋል፡፡ ክልሉ አሁን ወደ ተረጋጋ ሁኔታ ገብቷል ነው ያሉት፡፡ ክልሉን እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የማፍረስ ተልእኮ ከሽፏልም ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ በመግለጫቸው፡፡
አብዛኛው የክልሉ አካባቢ ሰላም መኾኑን ያነሱት ርእሰ መሥተዳድሩ የቀሩት ጥቂት ወረዳዎችም ሕዝብን በማስተባበር ወደ ሰላም እንዲመለሱ እንሠራለን ነው ያሉት፡፡ ክልሉን ሰላም የማድረግና መልክ የማስያዝ ሥራ በተከታታይነት እንደሚሠራም አመላክተዋል፡፡ “ክልሉ አሁን ላይ በጣም በተሻለ የጸጥታ ሁኔታና ወደ ነበረበት ሰላም እየተመለሰ መኾኑን ለሕዝባችን ማብሰር እወዳለሁም” ብለዋል፡፡
ክልሉ ወደ ሰላም እንዲመለስ መላው የክልሉ ሕዝብ ከፍተኛ ርብርብ ማድረጉንም አስታውቀዋል፡፡ በሀሰት ፕሮፓጋንዳ ተደናግረው የነበሩ አካላትም አሁን ላይ ሰላምን የማስፈን ሥራ እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ሕዝቡ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር ኾኖ እየሠራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ወጣቶች ሰላም እንዲመጣ ላደረጉት ጥረት አመሥግነዋል፡፡ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ተለይተው ያደሩም ኾኑ አዳዲስ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ሊፈቱ የሚችሉት በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የጥያቄዎቹ መፍቻ መንገድ ውይይትና ምክክር መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ ሕዝቡ እያደረገው ባለው ውይይትም ጥያቄዎች በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ እየጠየቀ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ የቆዩም ኾኑ አሁናዊ ችግሮች የሚፈቱት በክልሉ መንግሥትና በሕዝባችን ትብብር እንደኾነ ግልጽ ሊኾን ይገባል ነው ያሉት፡፡
የክልሉ መንግሥት የክልሉን ሕዝብ መብትና ጥቅም ለማስከበር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከሕዝብ ጋር በተመባበር በትኩረት ይሠራልም ብለዋል፡፡ በሀገር ደረጃ የሚፈቱ ጥያቄዎችም በምክክር እንዲፈቱ ጥረት ይደረጋል ነው ያሉት፡፡ የአማራ ክልል ሕዝብ ሀገር ወዳድ ሕዝብ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ሀገሩን መገንባት ይፈልጋል፣ የሕዝቦች ሰላማዊ ትስስር እንዲኖር ይፈልጋል፣ በየትኛውም አካባቢ ተንቀሳቅሶ መኖርና መሥራት ይፈልጋል፣ ከሁከትና ከብጥብጥ እንደማያተርፍ ጠንቅቆ ያውቃልም ብለዋል፡፡
ሕዝቡ በሚናፈሱ አሉባልታዎች ሳይታለልና ሳይወናበድ ችግሮቹን ሕጋዊና ሰላማዊ በኾነ መንገድ እንዲፈታ ግጭት ፈጣሪዎችን እረፉ ሊላቸው እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ ክልሉ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲገባ የጸጥታ መዋቅሩ የከፈለው መስዋእትነት ከፍ ያለ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ባለፉት ዓመታት ለአማራ ክልል የከፈለው መስዋእትነት የቅርብ ጊዜ ትውስታ መኾኑንም አስታውሰዋል፡፡ ለሀገር መብትና ጥቅም የቆመን ኀይል ስም ማጥፋት እና የኾነ አካል ብቻ አድርጎ መቁጠር ስህተት መኾኑንም አንስተዋል፡፡ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን መኾኑን ሕዝባችን ይገነዘባል፣ ተገንዝቧል፣ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር እየተመካከረ ሰላሙን እያስከበረ ነው ብለዋል፡፡
ክልሉ እንዲረጋጋ ላደረጉ የፖለቲካና የጸጥታ መሪዎችም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ መሪዎች መደበኛ ሥራዎችን ወደ ጎን ትተው ሰላምን ለማስፈን መሥራታቸውንም ተናግረዋል፡፡ የመንግሥት መዋቅርም ከፍተኛ መስዋእትነት መክፈሉንም ገልጸዋል፡፡ የተጀመረው ሰላም እንዲጸና እና የበለጠ ዘላቂ እንዲኾን የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!