
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የክልሉ ጸጥታ መዋቅርና የሀገር መከላከያ ሠራዊት በቅንጅት ባደረጉት ሕግ የማስከበር ሥራ ክልሉን ወደ አንጻራዊ ሰላም መመለስ ተችሏል ተብሏል።
የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ የክልሉን ወቅታዊ የሰላምና ደህኅንነት ጉዳይ አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መረጃ ሰጥቷል። መረጃውን የሰጡት በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማእረግ የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው ክልሉ በተደረገው ሕግ የማስከበር እርምጃ ወደ አንጻራዊ ሰላም መመለስ ተችሏል ብለዋል።
ኀላፊው እንዳሉት ውስጣዊ ችግርን በንግግር መፍታት እየተቻለ የክልሉ ኅብረተሰብና መንግሥት ባላሰበውና ባልጠበቀው ሁኔታ ነፍጥ ባነሱ ኃይሎች በተከፈተ ግጭት ክልሉ ወደ ሁለንተናዊ ቀውስ መግባቱን ተናግረዋል።
የትኛውንም አመለካከት፣ የትኛውንም ጥያቄና ሃሳብ በሕግና ሥርዓት ማቅረብ የሚሻው የአማራ ሕዝብ በየደረጃው ካለው የመንግስት የጸጥታ አካላት ጋር ለሰላም እርብርብ እያደረገ ከታቀደው የከፋ ብጥብጥና ጥፋት መታደግ ተችሏል ነው ያሉት።
አሁን ላይ የጸጥታ አካሉ እራሱን እያደራጀና እየተቀናጀ ግጭት የነበረባቸውን አካባቢዎች ወደ ቀደመ ሰላማቸው እየመለሰ ነው ብለዋል።
ማኅበረሰቡም መደበኛ እንቅስቃሴውን እየከወነ ነው ብለዋል አቶ ደሳለኝ።
የተፈጠረው ግጭት የክልሉን ሕዝብ ለአልተገባ ቀውስና ብጥብጥ ዳርጓል ነው ያሉት በሰጡት መረጃ።
በክልሉ በተፈጠረው አለመረጋጋትና ግጭት የክልሉን ርእሰ ከተማ ባሕር ዳርን ጨምሮ በክልሉ በተለያዩ ዞንና ወረዳዎችን የጦርነት ቀጠና ያደረገው ይህ ግጭት አሁን ላይ በተደረገው የጸጥታ መዋቅርና የክልሉ ሕዝብ ርብርብ መቀልበስ ተችሏል ብለዋል።
አሁን ላይ በአንዳንድ አካባቢዎች ያለውን ግጭትም ለማስቆም እየተሥራ እንደኾነ ነው የተናገሩት።
በተጀመረው ርብርብ ሁሉም አካባቢ ሰላምና ጸጥታው እንዲረጋገጥ ኅብረተሰቡ ለጸጥታ አካላት ያለውን ትብብር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
የክልሉ መንግስት ለሰላም ሁሌም ደጁ ክፍት ነው ያሉት አቶ ደሳለኝ ለክልሉ ሕዝብና ለሀገር ሰላም ሲባል ማንኛውንም ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ መፍታትን ያስቀድማል ነው ያሉት።
በመደማመጥ፣ በመተሳሰብና በመተጋገዝ የአማራን ሕዝብ ጥያቄዎች ማስመለስ፣ችግሮችንም መፍታት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
በነፍጥ የበለጠ ጥፋት እንጂ መፍትሔ ማምጣት እንደማይቻል መረዳት ይገባል ነው ያሉት።
ወንድም ወንድሙን መግደል፣ ክልሉን መሪ ማሳጣት፣ ሕዝብን ለጦርነት ሰለባ መዳረግና ለሁለንተናዊ ጥፋት ማወጅ እራስን መብላት ነው ያሉት ኀላፊው ለውጭ ጠላትም መጠቀሚያ መኾን አይገባም ብለዋል።
ለአማራ ሕዝብ ሰላምና ደኅንነት፣ ለክልሉ ልማትና እድገት የኃይል አማራጭ አይኾንም ያሉት አቶ ደሳለኝ በሰላም፣ በሕግና ሥርዓት ችግርን በንግግር መፍታትን ማስቀደም ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!