ኢትዮጵያን ከቴክኖሎጂ ጥገኝነት ለማላቀቅ እና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለቤት ለማድረግ የሚያግዝ ሀገር አቀፍ የአቪዬሽን ኢኖቬሽን ኤክስፖ ሊካሄድ ነው።

68

አዲስ አበባ: ጳጉሜ 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ፈጠራ ፣ ለአቪዬሽን ልህቀት በሚል መሪ መልእክት በሳይንስ ሙዚየም ከጥቅምት 13 እስከ 17/ 2016 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የአቪዬሽን ኢኖቬሽን ኤክስፖ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን እና የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በጋራ በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል።

በአቪዬሽን ፈጠራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች እና ልዩ ልዩ አካላትን ዕውቅና በመስጠት ፤ በመደገፍና በማበረታታት የአቪዬሽን ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን እንዲስፋፋ ያለመ መኾኑ ነው የተብራራው።

በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ ሀገር አቀፍ የአቪዬሽን ኢኖቬሽን ኤክስፖው የፈጠራ ክህሎት ያለው ባለሙያ ለማፍራት ትልቅ ድርሻ እንዳለው እና በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎች ላይ መንግሥት እገዛ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።

የቀጣዩን ትውልድ የአየር ትራስፖርት ሥርዓት ለማልማት ፣ ለመምራትና ለማስቀጠል እንዲቻል በተደራጀና በመዋቅር የተደገፈ የማበረታቻ ማዕቀፍ መዘርጋት ወሳኝ መኾኑን ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል።

ኢትዮጵያን በአህጉር ደረጃ የአቪዬሽን ኢኖቬሽን ማዕከል ለማድረግ የሚያስችል ሥራ እየተሠራ መኾኑን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው መንግሥቴ ገልጸዋል።

ከቴክኖሎጂ ጥገኝነት ለመላቀቅ በተራዘመ ሂደትም ቢኾን የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለቤት መኾን እንደሚገባ ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

በቴክኖሎጂ እና በኢኖቬሽን ዘርፍ ውድድር እና ሽልማት እንደሚኖርም ተገልጿል።

ሀገር አቀፍ የአቪዬሽን ኢኖቬሽን ኤክስፖው የፈጠራ ባለሙያዎችን ከኢንዱስትሪ ጋር ለማስተሳሰር እንደሚያግዝም ተገልጿል።

ዘጋቢ:- ዳንኤል መላኩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አብዛኛው የክልሉ አካባቢ ሰላም ሆኗል” ርእሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ
Next articleበአቶ ደመቀ መኮንን የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ሞቃዲሾ ገባ።