
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ በወቅታዊ ክልላዊ ጉዳዮች መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸውም የአማራ ክልል ባለፉት ሳምንታት የፀጥታ ችግር ውስጥ እንደነበር ተናግረዋል። በክልሉ የተከሰተው ቀውስ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት አስከትሏል። በተለይም በምሥራቅ ጎጃምና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል ብለዋል።
በፀጥታ መዋቅሩ፣ በሰላም ወዳዱ ሕዝብና በፖለቲካ መሪዎች የክልሉ የፀጥታ ሁኔታ ወደ ሰላማዊ ሁኔተ መድረሱንም ገልጸዋል። ክልሉን የማፍረስ ሴራ ከሽፏልም ብለዋል። አብዛኛው የክልሉ አካባቢ ሰላም ሆኗል፣ የቀሩት ጥቂት አካባቢዎች በሚቀጥሉት ቀናትና ሳምንታት ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለሱ ይሠራል ነው ያሉት።
አሁን ላይ ፊት ለፊት ከሚደረግ ውጊያ ወጥቶ የሽምቅ ውጊያ እንዳለም ተናግረዋል። ይህንም ለማስቀረት ይሠራል ነው ያሉት። ክልሉ አሁል ላይ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እየተመለሰ መሆኑንም አስታውቀዋል። መላው የክልሉ ሕዝብ ሰላሙ እንዲመለስ ርብርብ ማድረጉንም ገልፀዋል።
የክልሉ ሕዝብ ሰላም እንዲሆን ከፀጥታ ኃይሉ ጋር ሆኖ እየሠራ መሆኑን ነው የገለፁት። ሕዝቡ እያደረገ ላለው አስተዋፅዖም አመስግነዋል።
የአማራ ሕዝብ ያደሩ ጥያቄዎች በውይይትና በሕጋዊ መንገድ መፈታት ይገባቸዋልም ብለዋል። ጥያቄዎች በክልሉ ሕዝብና መንግሥት ቅንጅት እንደሚፈቱም አስገንዝበዋል። የክልሉ ሕዝብ ጥያቄ እንዲፈታ የክልሉ መንግሥት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ለመፍታት ይሠራል ነው ያሉት።
የአማራ ሕዝብ ሀገር ወዳድ ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ ከግጭት ትርፍ እንደሌለ ጠንቅቆ እንደሚረዳም ገልጸዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት የከፈለው መስዋእትነት የሚደነቅና ምስጋና የሚገባው መሆኑንም አንስተዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት የአማራ ሕዝብ በደረሱበት ችግሮች ሁሉ ሲደርስ የነበረ፣ ለሕዝብ ጥቅምና መብት ሲያስከብር መቆየቱንም አስታውሰዋል።
መከላከያ ሠራዊት የሀገር እንጂ የአንድ ግለሰብ ወይም የአንድ ማኅበረሰብ አይደለም፣ ይህንም ሕዝባችን ይሄን ጠንቅቆ ያውቃል ነው ያሉት። የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በአልተገባ መንገድ መወንጀል አግባብ አለመሆኑንም አንስተዋል።
የፖለቲካ መሪዎች ክልሉ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለስ ላደረጉት አስተዋፅኦ አመስግነዋል። የጀመሩትን ሥራ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!