“በጎንደር እና አካባቢው የጥምቀት በዓል ላይ ከ2 ሚሊዮን በላይ ታዳሚዎች ይገኛሉ፡፡” ባህልና ቱሪዝም ቢሮ

281

ባሕር ዳር ጥር 7/2012ዓ.ም (አብመድ) የዘንድሮ የጥምቀት በዓል በልዩ ድምቀት የሚከበር መሆኑን የአማራ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡

ለቱሪዝም ዕድገቱ በክልሉ ያለው የሠላም ሁኔታ አስተማማኝ ለማድረግ የክልሉ መንግሥት ከፌደራል መንግሥት ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑንም ቢሮው አስታውቋል፡፡ የአማራ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ የጥምቀት በዓል አከባበርን ምክንያት በማድረግ ዛሬ ጥር 07/2012 ዓ.ም መግለጫ ሰጥቷል፡፡ በዓሉ በተለይ በጎንደር፣ በላል ይበላ ፣ በምንጃር ሸንኮራ እና በሌሎችም አካባቢዎች በድምቀት ይከበራል፡፡

የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሙሉቀን አዳነ (ዶክተር) የጥምቀት በዓል በሠላማዊ መንገድ እንዲከበር ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ በየአካባቢው የተደራጁ ወጣቶች በዓሉ በሠላም እንዲጠናቀቅ ዘብ መቆም እንዳለባቸውም ኃላፊው አሳስበዋል፡፡

በጎንደር እና አካባቢው የጥምቀት በዓል ላይ የውጭና የሀገር ውስጥ ጎብኝዎችን ጨምሮ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ታዳሚዎች እንደሚገኙም ዶክተር ሙሉቀን በመግለጫቸው አመላክተዋል፡፡

የጥምቀት በዓል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) መመዝገቡ በርካታ ጎብኝዎች ወደ ኢትዮጵያ እና ወደ አማራ ክልል እንዲመጡ ምክንያት ይሆናል፡፡
“በዩኔስኮ የመመዝገቡ ትልቁ ቁምነገር ገንዘብ ለማግኘት ሳይሆን የእኛን ባህል እና ዕሴቶች ለሌሎች የምናስተዋውቅበት መሆን አለበት” ብለዋል ዶክተር ሙሉቀን በመግለጫቸው፡፡

ዘጋቢ፡- ብሩክ ተሾመ

Previous articleበዓላቱን በሰላም ለማክበር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
Next articleየተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ መኖሪያቸው ለመመለስ የሚያስችል እርቀ ሰላም እየተካሄደ ነው፡፡