
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጀነራል ተመስገን ጥሩነህ የመስዋዕትነት ቀንን አስመልክቶ ለጸጥታ አካላት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት መስዋዕትነት አንድን ከፍ ያለ ዓለማ ለመከወን ሲባል ጊዜን፣ ጉልበትን፣ ገንዘብን፣ ቤተሰብን እና ሕይወትን ጭምር ማጣት ነው፡፡ ሀገር ያለመስዋዕትነት ከማይፈጠሩ ጉዳዮች ቀዳሚዋ እንደኾነች ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ በየትኛውም ዓለም በስጦታ የተገኘ ሀገር አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡
የአለፈው ትውልድም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ፣ ሀገረ መንግሥቷን ለማጽናት እና የተሻለ ሥርዓት ለመፍጠር ዋጋ ከፍሏል ብለዋል፡፡
የውጭ ባዕዳን የሀገርን ሕልውና አጥፍቶ በቅኝ ግዛት ሕዝብን ለባርነት ለመዳረግ በተደጋጋሚ የፈጸመውን ወረራ በከፍተኛ መስዋዕትነት መቀልበስ መቻሉን አስታውሰዋል።
በኢትዮጵያ ለሀገራቸው መስዋዕትነትን የከፈሉ እንዳሉ ሁሉ ከሀገር ጥቅም ይልቅ የራሳቸው ጥቅም ከበለጠባቸው ባንዳዎች ጋርም ታግለው መስዋዕትነት ከፍለዋል ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ፡፡
“መስዋዕትነት ከፋዮች እየበዙ መስዋዕትነት አስከፋዮችን በማክሰም የሀገሪቱን ዕድገት እና ሀገረ መንግሥት በጽኑ መሠረት ላይ ይቆማል” ብለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ መላው ሕዝብ ከጸጥታ ሃይሉ ጋር መቆም ይገባዋል ብለዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!