
ባሕር ዳር: ጳጉሜ 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ጳጉሜን 2 የመሥዋእትነት ቀንን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫውን የሰጡት በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማእረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪና የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው እንዳሉት “ለሀገርና ለሕዝብ የሚከፈል መሥዋዕትነት ታሪክ የማይረሳው የትውልድ አሻራ ነው” ብለዋል
ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር፣ ፍትሕን ለማስፈንና ሀገርና ሕዝብን ለመጠበቅ ሁሉንም አይነት መሥዋዕትነት የከፈሉ በየደረጃው ያሉ የጸጥታ አካላትን በዛሬው ቀን ማውሳትና ማመስገን ተገቢ ስለመኾኑም ነው የተናገሩት። እናም “ለሕዝብ ደህንነና ሰላም ሲባል መሥዋዕትነት የከፈላችሁ በየደረጃው ያላችሁ የጸጥታ አካላት ሁሉ ምሥጋና ይገባችኋል” ነው ያሉት ኀላፊው። ለአማራ ሕዝብ የዋላችሁት ውለታ ታሪክ የማይረሰው ነው ፤ ከራስ በላይ ለሀገር ከራስ በላይ ለሕዝብ የመቆም ምሳሌ ናችሁ ብለዋል።
ተምሳሌትነታችሁ ሁሉም ለሕግ የበላይነት እንዲተጋ የሚያደርግ ነው ያሉት ኀላፊው ተልእኳችን ለሕግ ማስከበር ብቻ ሳይኾን ሰላምን ማደስ መጠበቅና ማሳደግ ጭምር ነው ብለዋል። የሚያጋጥሙ ችግሮችን ሁሉ በመተባበበርና በመተጋገዝ በአንድነት እንሻገራቸዋለን ነው ያሉት አቶ ደሳለኝ። በአዲስ ዓመት ማግስት የመሥዋዕትነትን ቀን ስናስብና ስናከብር የሀገርና ሕዝብ ቃልኪዳናችን በማደስ ነው ብለዋል።
አስተዋዩ የክልሉ ሕዝብም ለሰላም መስፈን ከጸጥታ ኀይሎቻችን ፣ ከሠራዊታችን ጋር ያደረገው ተባባሪነት የሚመሠገን ነው ያሉት አቶ ደሳለኝ አሁንም ሁለንተናዊ ድጋፉን አጠናክሮ እየቀጠለ ነው ብለዋል። በቀጣይ ለሚከበር የበዓል ኩነት የጸጥታ አካሉን ለመደገፍ ርብርብ እያደረገ ነው ብለዋል።
እስካሁን ባለውም 120 ሚሊየን ብር የሚገመት የእርድ እንስሳት ፤ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ለልዩ ልዩ ቁሶች አዋጥቷል ነው ያሉት። ክልሉ ከገጠመው የሰላም እጦትና ግጭት ወጥቶ ወደ ቀደመ ሙሉ ሰላም እንዲመለስም አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!