የዝናብ እጥረት የአደጋ ስጋት መፍጠሩን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አስታወቀ።

46

ሰቆጣ: ጳጉሜን 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በብሔረሰብ አስተዳደሩ በተለይም ሰሀላ ሰየምት ወረዳ በዝናብ እጥረት ምክንያት በሰው እና በእንስሳት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ቀድሞ ለመከላከል ከአጋር ድርጅቶች ጋር እየተሠራ መኾኑም ተገልጿል።

በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በዘንድሮ ክረምት የዝናብ ስርጭቱ የተስተከከለ አይደለም። በስሃላ ሰየምት ወረዳም የዝናብ እጥረት በመከሰቱ በሰውና እንስሳት ላይ ችግሮች አጋጥመዋል። ወረዳው ከ8 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በዘር ቢሸፈንም በዝናብ እጥረት መጎዳቱን የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

በወረዳው አቅኝ ቀበሌ ተገኝቶ አሚኮ ያነጋገራቸው አርሶ አደር 50 አለቃ ብርሃኑ ገብረ ማርያም ከግንቦት ጀምሮ በዘር የሸፈኑት ማሳቸው በዝናብ እጥረቱ ምክንያት አለመብቀሉን ገልፀዋል። በዝናብ እጥረቱ ምክንያት የእንስሳት መኖ እጥረት መፈጠሩን ተከትሎ እንስሳቶቻቸውን ከቀያቸው አስለቅቀው ወደ አጎራባች ወረዳዎች ማሸሻቸውን ገልፀዋል።

ሌላኛው አርሶ አደር ቄስ አዳነ አስረሴ በመኖ እጥረት እንስሳቶቻቸው እየሞቱባቸው መሆኑን ገልፀዋል።

የስሃላ ሰየምት ወረዳው በዘንድሮ ክረምት በ13ቱም ቀበሌ ከ8 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በዘር ሸፍኖ የቆየ ቢሆንም ዝናብ ባለማግኘቱ ሳይበቅል መቅረቱን የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማስረሻ መኮነን ተናግረዋል። ኃላፊው በወረዳው ከ100 ሺህ በላይ የዳልጋ ከብት፣ ከ4 ሺህ በላይ በግና ፍየል እንዲሁም ከ22 ሺህ በላይ የጋማ ከብቶች እንደሚገኙ ገልጸዋል። የእነዚህን ህይወት ለማሳለፍ ከመስከረም ወር እስከ ሰኔ ወር ድረስ የሚያቆይ ከ8 ሚሊዮን ቶን በላይ መኖ ያስፈልጋል ነው ያሉት ኃላፊው።

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምህረት መላኩ በብሔረሰብ አስተዳደሩ የዝናብ ስርጭቱ የተቆራረጠ ቢሆንም በዝቋላ ወረዳ 7 ቀበሌዎች፣ በአብርገሌ ወረዳ 6 ቀበሌዎችና ስሃላ ሰየምት ወረዳ ሙሉ በሙሉ የዝናብ እጥረት እንደተከሰተባቸው ገልፀዋል። የዝናብ ስርጭቱ ካለባቸው ወረዳዎች ላይም አልፎ አልፎ በበረዶ ጉዳት እየደረሰ መኾኑን ነው የተናገሩት። አቶ ምህረት በስሃላ ሰየምት ወረዳ ከ20 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል፤ ከ1200 በላይ እንስሳቶች በመኖ እጥረት መሞታቸውንም ተናግረዋል።

ኃላፊው ችግሩን ከሰውና ከእንስሳት ላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ለመከላከል ከአጋርተቋማትና በብሔረሰብ አስተዳደሩ የሚገኙ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር እቅድ አውጥተው እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል። ድርቅ የተከሰተባቸው ወረዳዎችን የሰውንም የይሁን የእንስሳትን ህይወት ለመታደግ አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ኃላፊው ገልጸዋል።

ዘጋቢ:–ሰሎሞን ደሴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየመሥዋዕትነት ቀን በመሥዋዕትነት የምትጸና ሀገር ኢትዮጵያ በሚል መሪ መልእክት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት እየተከበረ ነው።
Next article“ለሕዝብ ሰላምና ደህንነት ሲባል ሁሉንም አይነት መሥዋዕትንት የከፈላችሁ የጸጥታ አካላት ሁሉ ምሥጋና ይገባችኋል” አቶ ደሳለኝ ጣሰው