“ጀግኖች ጠበቁሽ፣ ጸንተው አጸኑሽ”

60

ባሕር ዳር: ጳጉሜን 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኃያል ጀግኖች ጠበቁሽ፣ በመከራ ጸንተው አጸኑሽ፣ በመስዋዕትነታቸው አስከበሩሽ፣ በደምና በአጥንታቸው የማትደፈሪ አደረጉሽ፤ በጠላቶችሽ ፊት አላቁሽ፣ ውድቀትሽን በሚመኙልሽ ፊት ከፍ ከፍ አደረጉሽ፣ መጥፋትሽን በሚያልሙት ፊት አደመቁሽ፣ በታሪክ ብራና ላይ አረቀቁሽ፡፡ በማይናወጽ የክብር ዙፋን ላይ አስቀመጡሽ፡፡ የመከራ ባሕር የምትከፍይበት በትር አስጨበጡሽ፣ ለዘመናት የሚጸና የክብር ዘውድ ደፉልሽ፣ ግርማው የማይገፋ የመወደድ ካባን ደረቡልሽ፣ ለዘመናት ጠብቀው ለልጅ ልጅ አስረከቡሽ፡፡

በረሃውን አይፈሩትም፣ በረዶውንም አያስታውሱትም፣ እሾህና አሜካላውንም አይሰቀቁትም፣ ጦርና ጎራዴውንም አይደነግጡለትም፣ እንደ ሰማይ መብረቅ የሚያጓረውን የጦር ፍላጻ አይሸበሩለትም፤ ስምሽን አንግበው፣ ሠንደቅሽን አስቀድመው በሞት መካከል ይረማመዳሉ፣ በጠላት ፊት እንደ አንበሳ ያገሳሉ፣ እንደ ነብር ይቆጣሉ፣ ከሁሉም ልቀው ጠላቶቻቸውን ይጥላሉ፣ ኃያላን ነን የሚሉትን ይሰብራሉ፣ ወንድ ከእኛ በላይ የሚሉትን ያንበረክካሉ፣ ሠንደቋን በጠላት ሠፈር በኩራትና በድል አድራጊነት ያውለበልባሉ እንጂ፡፡

የሀገር ፍቅር የሚያንገበግባቸውን፣ የሀገር ክብር እንቅልፍ የማያስተኛቸውን ጀግኖች ችሎ የሚገፋቸው፣ ሆኖለት ድል የሚመታቸው አይገኝም፡፡ ሀገር የነካውን፣ ድንበር የሠሰረሰውን ሁሉ ከምሽግ ምሽግ እየተረማመዱ ይቀጡታል፣ አቀቡትን እየወጡ፣ ቁልቁለቱን እየወረዱ መድረሻ ያሳጡታል፣ ምድራቸው የማትነካ እንደሆነች ያሳዩታል፡፡

ኢትዮጵያ ዓልሞ ተኳሶች የሚወለዱባት የጀግኖች ምድር ናት፡፡ ኢትዮጵያ ለክብሯ እልፍ የሚሰዋላት የጽኑዎች ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ ጀግኖች ለፍቅሯ ደምና አጥንት የሚገብሩላት የጀግኖች እናት ናት፡፡ ኢትዮጵያ በልጆቿ መስዋእትነት በጠላት ፊት ግርማን እንደተላበሰች የኖረች ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ በዘመኗ መሸነፍን ያላወቀች፣ ድል አድራጊነትን የእርሷ መገለጫ ያደረገች ታላቅ ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያን የሚገፋት ወድቋል፣ የሚሰልላት አልቋል፤ የሚተናኮሏት ደቅቋል፡፡ እርሷ በመስዋእት የሚጠብቋት፣ በደመና በአጥንት የሚያጥሯት ሀገር ናትና፡፡

ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ሀገራቸውን የሚወር ጠላት መጣ በተባ ጊዜ ፈጽሙ አይሸበሩም፤ አይደነግጡም፡፡ ይልቅስ ድል እንደሚመቱት፣ በወንዝና በሸንተረራቸው እንደሚያስቀሩት ያውቃሉ እንጂ፡፡

አዶልፍ ፓርለሳክ ስለ ኢትዮጵያውያን ጀግንነት ሲጽፉ ጠላት ወደ ኢትዮጵያውን በመጣ ጊዜ ጦር መጣ! ጦር መጣ! እያሉ አንዱ ለአንደኛው እያቀበለ ያስተጋባል፡፡ የሚፎክሩት ወታደሮች በውሏቸው ስንት የጠላት ወታደር አንገት እንደሚቀነጥሱ ጮህ ብለው እየፎከሩና እየሸለሉ ወደ ጦር ሜዳ ይንደረደራሉ ብለዋል፡፡

ተጫኔ ጆብሬ “የሐበሻ ጀብዱ” ብለው በተረጎሙት አዶልፍ ፓርለሳክ መጽሐፍ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በኢጣልያ ወረራ ጊዜ ያደረጉትን ተጋድሎ ሲጽፉ “ ወታደሮቻችን በድፍረትና በታላቅ ወኔ ወደ ፊት ይገፋሉ፡፡ የመጀመሪያው ረድፍ ገና ሳይተኩስ ይረግፋል፡፡ በመድፍና በመትረጊሶች እየታገዙ ጣልያኖች የኢትዮጵያውን ሠራዊት ከርቀት እየመቱት እነሱም ወደፊት ይገፋሉ፡፡ ይኼውም አልበቃ ብሎ እነዚያ አውሮፕላኖች ከመቼውም ጊዜ በላይ በጣም ዝቅ ብለው፣ ምን አልባትም የአውሮፕላኖቻቸው ጎማ የኢትዮጵያን ወታደር አናት እስኪነካ ድረስ ዝቅ በማለት በመትረየሶቻቸው የእኛን ጦር ያረግፉታል፡፡ ነጩ ጎርፍ (ነጭ ልብስ የለበሱ የኢትዮጵያ ወታደሮች) የወደቀውን የጦር ሜዳ ጓዱን እየዘለለ ወደፊት ይነጉዳል፡፡ አንዱ ሲወድቅ ሌሎች አሥሮች እየተተኩ፣ አስሮች ሲወድቁ ሌሎች ሃምሳዎች እየተተኩ የጣልያንን ጦር እንደ ደራሽ ውኃ አጥለቀለቁት፡፡

የኢትዮጵያ ሠራዊት ከጎኑና ከፊቱ የሚወድቀውን የጦር ሜዳ ወንድሙን እየዘለለ ሲጓዝ ከላይ ከተራራው ጫፍ ሌሎች በሺህ የሚቆጠሩ ተዋጊዎች ድንጋዩን እየዘለሉ፣ እየፎከሩና እየሸለሉ ወርደው ተቀላቀሉ፡፡ የማያልቅ የሠራዊት ጎርፍ፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሲወለድ ጀምሮ ጀግና ተዋጊ ነው፡፡ አንዴ ውጊያ ውስጥ ከገባ በዚህ ምድር ላይ ምንም የሚያቆመው ኃይል የለም ” ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ብቻ አይደሉም ጽኑ አማኞችም ናቸው እንጂ፡፡ ወደ ጦርነት እየሄዱ ታቦት ተሸክመው፣ ጸሎት እያደረሱ ይጓዛሉ፡፡ በእምነታቸው ጽናት እና በጀግንነት በብርታት ጠላቶቻቸውን ድል ይመታሉ፡፡ ተጫኔ ጆብሬ የአዶልፍ ፓርለሳክን “ የሐበሻ ጀብዱ” ብለው በተረጎሙት መጽሐፋቸው ላይ“ በጸሎታቸውም የሀገራቸውን ድንበር በማን አለበኝነት ደፍሮ የመጣን የጠላት ሠራዊት ከሀገራቸው ጠራርገው ያወጡ ዘንድ እግዚአብሔር ብርታቱን ሰጥቶ ይረዳቸው ዘንድ ሳይታክቱ በየምሽቱ ይለምናሉ፤ ይማጸናሉ፡፡ በእያንዳንዷ ምሽት በለስላሳና ለጀሮ በሚስብ ድምጽ የሚጀምረውን መዝሙር ወይም ቅዳሴ በየዋሻና በየቋጥኙ ሥር፣ በየጥሻው ውስጥ ያለው በመቶ ሺህ የሚቆጠረው ሻካራው የወንዶች ድምጽ ይቀበልና ሲደግመው፣ ከነሱ የገደል ማሚቶው ተቀብሎ ተቀብሎ በጣም ሩቅ ላሉት ሲያስተጋባ ይህ ነው ተብሎ መግለጽ የማይቻል ፍጹም ልብ የሚነካ ሰውነት የሚያንቀጠቅጥ ስሜት ይሰማል” ብለዋል፡፡

በግፍ ሀገራቸውን የወረረውን ጠላት ጦራቸውን ሰብቀው፣ ጎራዴያቸውን መዝዘው ለማባረር አምላክ እንደሚረዳቸው ያለ መጠራጠር ያምናሉ፡፡ በፍጹም እምነት፣ በጸና ጀግንነት ለመስዋእት ይጓዛሉ፡፡ በአመኑት አምላካቸው ረዳትነት፣ በእነርሱም ጀግንነት ጠላቶቻቸውን ድል ይመታሉ፡፡

ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በታላቅ ጀግንነት የጠላት ዘመናዊ መሳሪያ ሳያግዳቸው ጦራቸውን እየሰበቁ፣ ጎራዴያቸውን እየመዘዙ፣ እየፎከሩና እየሸለሉ፣ በታላቅ የጀግንነት ወኔ እየጮኹና እያጓሩ ዘለው ዘለው ከጠላት መካከል በመግባት የጠላትን ወታደር በጦራቸው እየሰነጠቁ፣ በጎራዴያቸው አንገቱን እየቀሉ፣ መውጫ መግቢያ፣ መድረሻ እያሳጡ ነው ሀገር ያጸኑት፡፡

“ሰው ቢሞት ፍቅር አይሞትም” እንዳሉ ሀዲስ ዓለማየሁ ለሀገር ፍቅር የተከፈለ መስዋእትነት ከዘመናት በኋላም ሕያው ሆኖ ይኖራል፡፡ ትውልድ አልፎ ትውልድ በተተካ ቁጥር ይዘከራል፡፡ ለትውልድም የልቡና ስንቅና ትጥቅ ይሆናል፡፡
ሀዲስ ዓለማየሁ ትዝታ በተሰኘው መጽሐፋቸው በኢጣልያ ወረራ ጊዜ ኢትዮጵያውያን ስለ ፈጸሙት ጀግንነት እና ለሀገር ፍቅር የከፈሉትን መስዋእት ሲጽፉ“ ከሁለቱም ወገን ተኩስ እንደተፋፋመ ሳለ ምንም ትዕዛዝ ሳይሰማ ፊትም፣ ኋላም ከተሰለፉት ኢትዮጵያውያን ብዙዎች አለቃና ጭፍራ እንደተማከሩ ሁሉ ባንድነት ‹ሆ› ብለው አውክተው በመንገድ ተመትተው የወደቁት ወድቀው የቀሩት ጣሊያኖች ምሽግ ውስጥ ገብተው የጨበጣ ጦርነት ገጠሟቸው፡፡ እዚያ ከኢትዮጵያውያን ሽጉጥ ያለው በሽጉጥ ሌላው በጎራዴና በጩቤ፣ ያ የሌለው በጠመንጃው አፈሙዝ፣ ጣልያኖች በሳንጃ፣ በእጅ ቦንብና ባላቸው መሳሪያ ሲጨፋጨፉ፣ ሲተራረዱ ከቆዩ በኋላ ጣልያኖች ምሽጋቸውን ለቀው ወደ ኋላ ሸሹ” ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያዊ ሠራዊት ላመነበት ሁሉ ለመሞት ይነጉዳል፣ መስዋእት ሆኖ ሀገሩን ያስከብራል፤ ጠላቱንም ያሳፍራል፡፡

ጀግንነት በኢትዮጵያ ምድር ማንነት ሆኖ የነበረ፣ የኖረ፣ ያለ እና የሚኖር እንጂ በአንድ ዘመን መጥቶ በዚያው የተቋጨ አይደለም፡፡ አንድ ትወልድ አልፎ ሌላ ትውልድ ሲመጣ ሌላ ጠላትም በሀገር ላይ ይነሳል፡፡ ከአባቶቻቸው ነጻነትን የተጎናጸፈች ሀገር የወረሱ ልጆችም እንደ አባቶቻቸው ሁሉ ዘራፍ ብለው ተነስተው የሀገራቸውን ጠላት ይመልሳሉ፡፡

ፍቅረሥላሴ ወግደረስ “እኛና አብዮቱ” በተሰኘው መጽሐፋቸው በኢትዮ ሶማሊያ ጦርነት የእናት ሀገር ጥሪ ሲቀርብ ሕዝቡ በእልህና በወኔ መነሳቱን ጽፈዋል፡፡ የወቅቱ ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የእናት ሀገር ጥሪ የሕዝቡን ወኔና ስሜት ቀሰቀሰ፤ ብስጭትም ቁጭትም አስከተለ፡፡ በሀገር ፍቅር የተቃጠው ሕዝብ ገንፍሎ ተነሳ፡፡ ለመዝመት ዝግጁ መሆኑን በየአቅጣጫው ገለጠ፡፡ የሕዝቡ መነሳሳት ከተጠበቀው በላይ ነበር ብለዋል፡፡

በዚያ ዘመን ኢትዮጵያ በሁሉም አቅጣጫ ተወጥራ ተይዛለች፡፡ ኅልውናዋም አጠያያቂ ሆኖ ነበር፡፡ በሀገር ፍቅር የዘመተው የኢትዮጵያ ሠራዊት ግን በቆራጥነት ተዋጋ፡፡ ጠላትንም እየደመሰሰ ወደ ፊት ገፋ፡፡ የሚከፈለውን መስዋእትነት ከፍሎ ኢትዮጵያን ነጻ አወጣ፡፡ ስሟንም ከፍ አደረገ፡፡ የሚደፍሯትንም አዋረደ፡፡

ኢትዮጵያ ጀግኖች በመስዋእት የጠበቋት፣ የሚጠብቋት፣ በብርቱ ክንዳቸው ያስከበሯት፣ የሚያስከብሯት፣ ጠላትና ሰላቶ የማይደፍራት ጽኑ ሀገር ናት፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የማር ምርት ካላቸው አሥር ሀገሮች አንዷ ነች” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleየመሥዋዕትነት ቀን በመሥዋዕትነት የምትጸና ሀገር ኢትዮጵያ በሚል መሪ መልእክት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት እየተከበረ ነው።