በዓላቱን በሰላም ለማክበር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

259

ባሕር ዳር ጥር 7/2012ዓ.ም (አብመድ) የከተራ እና የጥምቀት በዓላት በሠላም እንዲከበሩ የሚያስችል ዝግጅት ማድረጉን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

በኮሚሽኑ የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎትና የመንገድ ደኅንነት ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ሙሉ ሁነኛው እንዳስታወቁት በዓሉ በሠላም እንዲጠናቀቅ ለማድረግ ፖሊስ ተዘጋጅቷል፡፡

በክልሉ የከተራ እና ጥምቀት በዓላት በሚከበሩባቸው ከ14 ሺህ በላይ አድባራት ሠላማዊ እንቅስቃሴ እንዲኖር የጸጥታ ኃይሉ የተቀናጀ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉንም ነው የገለጹት፡፡

በዓሉ በሠላም እንዲጠናቀቅም የክልልና የፌደራል ጸጥታ አካላት በጋራ የሚሠሩበት አደረጃጀት ተፈጥሯል፡፡ የማኅበረሰቡን ለሠላም ዘብ የመቆም ልምድም በዓሉን በሰላም ለማክበር እንደ መልካም አጋጣሚ ጠቅሰዋል፡፡

ቅንጅታዊ አሠራሩን የበለጠ ለማጎልበት ከህዝቡ ጋር በየደረጃው ምክክር ሲደረግ መቆየቱንም ምክትል ኮሚሽነር ሙሉ አስረድተዋል፡፡ ይህም ሆኖ አጠራጣሪ ነገሮች ሲታዩ ማኅበረሰቡ በአቅራቢያው ላሉ የጸጥታ ኃይሎች ጥቆማውን ማድረስ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡-ኃይሉ ማሞ

Previous articleባሕር ዳር በጣና ላይ የጀልባ ትርኢትና በሌሎች መሰናዶዎች እንግዶችን ለማስተናገድ ተዘጋጅታለች፡፡
Next article“በጎንደር እና አካባቢው የጥምቀት በዓል ላይ ከ2 ሚሊዮን በላይ ታዳሚዎች ይገኛሉ፡፡” ባህልና ቱሪዝም ቢሮ