
ባሕር ዳር: ጳጉሜ 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ”በመሥዋዕትነት የምትፀና ሀገር”በሚል መሪ መልዕክት ጳጉሜን 2/2015 ዓ.ም እየተከበረ ነው፡፡
ብዙ ጀግና የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች የሀገራቸውን ዳር ድንበር አናስደፍርም ብለው ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰዋል፡፡ ለሀገራቸውም መሥዋዕትነትን ከፍለዋል፡፡ ትናንት ሀገርን ሊደፍር ሕግ ሊያፈርስና ድንበር ሊጥስ የመጣን የጣሊያን ሠራዊት አሳፍረው የመለሱት ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ለመሥዋዕትነታቸው ሌላ ምክንያት አልነበራቸውም፡፡ የመጀመሪያውም የመጨረሻውም ምክንያታቸው ሀገራቸው ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነበር፡፡ ከሞቀ ቤታቸው ወጥተው፣ ሚስት እና ልጆቻቸውን ትተው፣ እናት እና አባታቸውን ተሠናብተው በሰላም ከተመለሱ ሀገራቸው ውለታ ልትከፍላቸው ፣ ካልተመለሱ ግን መሥዋዕትነት ሊከፍሉላት የክት ልብሳቸውን ለብሰው ስንቃቸውን ቋጥረው፣ አጋሰሳቸውን ጭነው ከቤት ሲወጡ ልባቸው ውስጥ የተጠራቀመውን የሀገር ፍቅር በተግባር ለመግለጽ እንጂ ሌላ መነሻም መድረሻም አልነበራቸውም ነበር፡፡
ለቀናት ተጉዘው ከጦርነቱ ሜዳ ሲደርሱ የሚወረወረውን ጦር፣ የሚወርደውን ቦምብ፣ የሚመጣውን ኹሉ ለመቀበል የቆረጠው ልባቸው እንዳይሠሙት አድርጓቸዋል፡፡ ጠላታቸውን ፊት ለፊት ገጥመው ሲረፈርፉት በልባቸው ውስጥ የሚንቀለቀለው የሀገር ፍቅር ስሜት ላፍታ ወደ ኋላ እንዲሸሹ አልገፋፋቸውም፡፡ ጀግና ለሀገሩ ደሙን አፍስሶ አጥንቱን ከስክሶ ሕይወቱን ሲገብር ካሳው ከመቃብር በላይ የሚውለው ዘላለም የሚዘከረው ኢትዮጵያዊ ስሙ ብቻ ነው፡፡
ትናንት የተጀመረው መሥዋዕትነት እስከ ዛሬ ዘልቆ ዛሬም ወራሪ ጠላት ሀገር በወረረ ወቅት ሕጻን ፣ አዋቂው ፣ የተማረ ያልተማረው ፣ አራሽ ገበሬውም ይሁን ቀዳሹ ለሀገሩ መሥዋዕትነትን ከፈለ፡፡ ለዚህ ሀገርን በደሙ እና በአጥንቱ ላቆመው ኢትዮጵያዊ ክብር ይገባዋል ያሉን አርሶአደር በላይነህ ኃይሉ ናቸው፡፡
አርሶ አደር በላይነህ ለሀገር መሥዋዕትነት የከፈሉ ሰዎች ክብር ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ ቀደም ባሉት ነገሥታት ዘመን በጅምላ ይዘመት ነበር ያሉት አርሶ አደር በላይነህ ከኃይለ ሥላሴ ዘመን በክቡር ዘበኛ ፣ ኋላም በመከላከያ ሠራዊት በመተካቱ ኀላፊነቱን ተቀብሎ መሥዋዕትነትን እየከፈለ የሚገኝ እርሱ ነው ብለዋል፡፡ መከላከያ ሠራዊትን ማክበርና ለሀገር ሲሉ ያለፉትን መዘከር ይገባል “መሥዋዕትነት ለሀገር ሲባል የተከፈለ ዋጋ ነውና” ብለዋል፡፡
አርሶ አደር የማታ ቢሠጥ በበኩላቸው መከላከያ ሠራዊት ለሀገር ሲከፍለው ለነበረው መሥዋዕትነት ምሥጋና ይገባዋል ብለዋል፡፡ እነሱ ባይኖሩ ዛሬ እኛ ለዚህ አንበቃም ነበር ነው ያሉት፡፡ ኢትዮጵያ የጀግና ሀገር ናት ፤ ጀግና ይወለድባታል ፤ መከላከያ ሠራዊትም መሥዋዕትነትን ከፍሎ ጀግንነቱን እያስመሰከረ ነው፡፡ መከላከያ ሠራዊት ሀገሩን ጠብቆ ለትውልድ ለማስተለፍ በርትቶ እየሠራ ነው፡፡ በከፈለው መሥዋዕትንት ልክ ሊከበር፣ ሊወደስ እና ሊመሰገን ይገባል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡ ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!