
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ነጻነቷ እንዳይጣስ፣ ክብሯ እንዳይረክስ፣ ድንበሯ እንዳይገረሰስ እልፍ መስዋዕት ተከፍሎላታል፣ ለእርሷ የኖሩ ጀግኖች ሞተውላታል፣ ለእርሷ የኖሩ ጀግኖች ቆስለውላታል፣ ለእርሷ የኖሩ ጀግኖች ደምተውላታል፣ እርሷን ያሉ ልበ ሙሉዎች ላባቸውን አንጠፍጥፈውላታል፣ ተርበውላታል፣ ተጠምተውላታል፡፡
ስለ ክብሯ ጦር ወጋቸው፣ ስለ ስሟ የጥይት አረር መታቸው፣ ስለ ዝናዋ እሾህና አሜካላ አሰቃያቸው፡፡ እነርሱ ግን ጦሩን ረሱት፣ የጥይት አረሩን ስለ ሀገር ፍቅር ናቁት፣ እሾህና አሜካላውንም ተረማመዱት፡፡ እነርሱን መከራ አያስቆማቸውም፣ ፈተናም አይበግራቸውም፡፡ ሀገራቸውን ብለው፣ ሠንደቃቸውን አስቀድመው እየገሰገሱ ከጠላት ጋር ታገሉላት፣ ድል እያደረጉም አኖሯት፡፡ በመስዋዕትም ጠበቋት፡፡
እርሷ በመስዋእት የጸናች፣ በጀግኖቿ የታፈረች፣ በልጆቿ የተፈራች፣ ጠላቶቿን ያስገበረች፣ ድል የመታች፣ እንዳልነበሩ ያደረገች፣ ከእግሯ ሥር ጥላ እጅ ያስነሳች፣ በክብሯ የመጡባትን ኀያላኑን ያንኮታኮተች፣ ጭቁኖቹን ነጻ ያወጣች፣ ነጻነት የተነፈጋቸውን ነጻነትን የሰጠች ታላቅ ሀገር ኢትዮጵያ፡፡ የከበረው ስም እንዳይጎድፍ ደም እንደ ጎርፍ ፈስሶላታል፣ የገዘፈው ታሪኳ እንዳይንኳሰስ አጥንት ተከስክሶላታል፣ ውድ ሕይወት ተገብሮላታል፤ ብዙዎች ከአንቺ በፊት ያድርገን እያሉ ቀደሙላት፣ የመጣባትን ሞት ሞቱላት፣ የተቀዳላትን የሞት ጽዋ እነርሱ ተጎነጩላት፣ እነርሱ ወድቀው እርሷን አቆሟት፣ እነርሱ ተሰውተው በዓለት ላይ አጸኗት፡፡ የማትናወጽ አደረጓት፡፡ የኢትዮጵያ ጀግኖች ለዘመናት በመስዋዕትነታቸው ሀገራቸውን ከወራሪ ጠበቋት፣ ድል አድራጊ ብቻ አድርገው አስቀመጧት፡፡ በዓለም ታሪክ ፊት አገዘፏት፤ በቅኝ ገዢዎች ፊት አስፈሪ ግርማን ሰጧት፡፡ ለጥቁሮችም የጭንቅ ቀን ደራሽ እናት አደረጓት፡፡ ኢትዮጵያ የልጆቿ መስዋዕትነት ያቆማት፣ የልጆቿ ደምና አጥንት ያስከበራት፣ የአምላክ በረከትና ረድኤት የጠበቃት፣ የደጋጎች ጸሎትና ልመና ተድላን የማያሳጣት ጥንታዊትና ቀዳማዊት ሀገር ናት፡፡ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ትውልድ አልፎ ትውልድ በተተካ ቁጥር ጠላት ይነሳል፤ ያም ጠላት ድል ኾኖ ይመለሳል፡፡ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ለጠላት አሳልፈው አይሰጧትም፤ ሞትን እና መከራን ሸሽተውም አይተዋትም፣ ሞትን ንቀው፣ ኀያል መስዋዕት ከፍለው ነጻ ያደርጓታል፣ በድል አድራጊነት ያኖሯታል እንጂ፡፡ በረጅም ዘመን ታሪኳ ለጠላት ያልተበገረች ሀገር እንደኾነች ታሪክ ይዘክራል፤ ትውልድ ሁሉ ይመሰክራል፡፡
ጰውሎስ ኞኞ የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት በሚለው መጽሐፋቸው ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ ለሺህ ዓመታት የተደጋገመ ሙከራ ተድርጓል፤ ኢትዮጵያውያን ግን ሀገራቸውን በሌላ ባዕድ ሳያስይዙ ባላቸው ኀይል ሲከላከሉ ቆይተዋል፡፡ በአውሮፓም ኾነ በኤሲያ ወይም በአፍሪካ የሚነሱ ታላላቅ መንግሥታት ጉልበት እያገኙ ግዛታቸውን በሚያሰፉበት ጊዜ ኢትዮጵያንም ለመደረብ ብዙ ጊዜ ሞክረዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን ለማንም ሳይበገሩና ሳይገብሩ እስካሁን ሀገራችንን አስከብረው ቆይተዋል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያን አስገብሮ ለመያዝ የተደጋጋመ የውጭ ጦር ቢመጣም ኢትዮጵያውያን ባላቸው ኀይል የማይበገሩ ኾነው የሚመጣውን የውጭ ጦር ሁሉ መልሰዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን የማይለቁና የሌላ ሀገር የማይፈልጉ በመኾናቸው እንጂ ራሳቸውን ከማስከበር አልፈው ሌሎች ሀገራትን ደርበው የሚይዙባቸው እድልም ነበራቸው ብለዋል ጳውሎስ፡፡
ኢትዮጵያውያን ከዘመን ዘመን የሚሸጋገር አንድ እውነት አላቸው፡፡ በሀገር፣ በሚስትና በሃይማኖት ቀልድም፣ ድርድርም የለም የሚል፡፡ ኢትዮጵያዊ በሀገሩ በርሰቱ፣ በጎኑ በሚስቱ፣ በነብሱ መጽናኛ በሃይማኖቱ ከመጡበት ፈጽሞ አይታገስም፡፡ ፈጽሞም አይምርም፡፡ የማይነካውን ሲነኩበት፣ በማይመጣው ሲመጡበት ያን ጊዜ ቁጣው እንደ እሳት ይለበልባል፤ በትሩ እንደ መብረቅ ያይላል፡፡
ተክለጻዲቅ መኩሪያ ዓፄ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት በሚለው መጽሐፋቸው የሎንዶን ታይምስ ጋዜጣን ዋቢ አድርገው ሲጽፉ “ኢጣሊያኖች ወደ አፍሪካ ቅኝ ሀገር ለማግኘት ፊታቸውን ባዞሩበት ሰዓት በቀላል ሊያዝና ሊገዛ የሚችለው ክፍል ቀደም ብሎ ስለተያዘ ወደ አልተያዘው እና ወደ አስቸጋሪው ተመለከቱ፡፡ ኢጣሊያኖች ንጉሥ ምኒልክን ያሳመኑ መስሏቸው ሲታለሉ እርሳቸው ግን በመሳሪያ እየተዘጋጁ የአጻፋውን ኀይል አሳዩዋቸው፡፡ የእርሳቸውም ድል ማድረግ የመላ አፍሪካ ድል ነው፡፡ ይህም አይነቱ አስተያየት ወደፊት እያየለ ግልጽ ኾኖ የሚታይ ነው፡፡ በእነዚህ ሀገሮች (አፍሪካውያን) ዘንድ ወሬው በነፋስ ክንፍ በረሐውን ሁሉ አቋርጦ በፍጥነት የሚሮጥ ስለኾነ ከጫፍ እስ ጫፍ አሁንም ታውቋል፡፡ ወደፊትም አፍሪካ አውሮፓን ማሸነፉ ስለታወቀ ቁጥሩ ይኸን ያህል ሊገመት ለማይችለው የአፍሪካ ሕዝብ የሕይወት ንቃትና የመከላከል ሥሜት ያሳድራል፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ አደገኛ ስለኾነ በኢጣሊያኖች መሸነፍ ተደሳቾች መኾን ምቹ አይደለም፡፡ ይኽ መሸነፍ የሁላችንና የሌሎችም ጭምር መሸነፍ ነው፡፡ የሥልጣኔ መሸነፍም አይደለም፡፡ የቅኝ ሀገር ገዢ የኾነችውና የነገይቱም አውሮፓ መሸነፍ ነው” ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በብርቱ መስዋዕትነት ቅኝ ገዢዎችን ድል መትተዋልና ቅኝ ገዢዎችን ሁሉ አስደነገጡ፡፡ በቅኝ ለተገዙት ደግሞ አዲስ የምሥራች፣ አዲስ ብርሃንና የመውጫ ቀዳዳ ይዘው መጡ፡፡ ኢትዮጵያ በድል አድራጊነቷ በዓለም ተከበረች፡፡ ይህንም ያመጣው የልጆቿ መስዋዕትነት ነው፡፡ ኮሎኔል አልኸንድሮ ዴል ባዬ የጻፉትና ዶክተር ተስፋዬ መኮንን “ ቀይ አንበሳ” ብለው በተረጎሙት መጽሐፍ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በኢጣልያ ወረራ ወቅት ያሳዩት ጽኑ ጀግንነት ድንቅ እጹብ የሚያሰኝ እንደነበር ተመዝግቧል፡፡ እኒያ ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር አብረው የዘመቱት ኮሎኔል አልኸንድሮ የኢትዮጵያ ጀግኖች በሀገራቸው ጉዳይ ለሰከንድ እንኳን ዓይናቸው የማይከደን፣ ወኔያሞች፣ ቆራጥና ጀግና ጦረኞች ናቸው ብለዋል፡፡ የመርዝ ቦንብ ያዘሉ የጠላት አውሮፕላኖች በማይደረስባቸው ከፍታ ላይ ኾነው የሚለቁት ቦንብ ቁልቁል ያለ ችግር ይምዘገዘጋል፡፡ አንዳንዶቹም ሲወርዱ እንደ አውሎ ነፋስ የሚጋፋ አየር ይፈጥራሉ፡፡ መሬቱን ሲነኩም ፍንዳታው ይሰማል፡፡ አፈር፣ ጭስ፣ የቦንብ ፍንጣሪ፣ በየአቅጣጫው በመበታተን የእነዚህን የንጹሕ ዜጎች፣ ለሀገራቸው ሟቾች ጦረኞች አካላቸውን እየቆራረጠ እንደ ቦንብ ፍንጣሪ በየቦታው ሲጥል ይታያል፡፡ በዚህ የማያቋርጥ የእሳት ነበልባል ውስጥ ወደፊት መገስገሳችን ቀጠልን፡፡ የሚደርስባቸው ጭፍጨፋ ከዓላማቸው ምንም ሊያዘናጋቸው እና የዚህች ሀገርን ልጆች ሊያግዳቸው አልቻለም ብለዋል ኮሎኔል አልኸንድሮ፡፡
ኮሎኔሉ የኢትዮጵያውያንን ጀግንነት እና ለመስዋዕት መዘጋጀትን ሲገልጹ ከጠላት በኩል ያለማቋረጥ የሚተኮሱት መሳሪያዎች እሳት ይተፋሉ፡፡ ምንም ሊገታቸው የማይችለው የኢትዮጵያ ጀግኖች ግን ፊት ለፊት ይገሰግሳሉ፡፡ የሚዘንብባቸውን የጥይት ናዳም ከቁም ነገር ሳይቆጥሩ ይጓዛሉ፡፡ የእነዚህን የጥቁሮች የአፍሪካ ምድር ልጆች ወደፊት መገስገስን በጥይት ናዳ ለማቆም መሞከር ልክ የአንድን ወራጅ ውኃ ቁልቁል መፍሰስ በመድፍ ደብድቦ ለማቆም እንደመሞከር ይቆጠራል፡፡
ኢትዮጵያውያን ጠላት ሲያይልና ይበልጥ ሲያጠቃቸው ጀግንነታቸው እና የውጊያ ስሜታቸው ይበልጥ ይጨምራል፡፡ ይባባሳል፡፡ ለተሰነዘረባቸው ጥቃት የሚተኮስባቸው ጥይት ምንም ሳያስጨንቃቸው ተወርውረው እየተንደረደሩ ወደ ጠላት ምሽግ በመሮጥ ጥይት እያፈተለከችበት የምትወጣበትን አፈሙዝ በመጨበጥ ከምንጩ ማድረቅ ነው ዋና ዓላማቸው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያኖቹ ጠላት እንዲጠጋቸው ዝም ይሉታል፡፡ በተጠጋቸውም ጊዜ ከፍተኛ ጀግንነት በተሞላበት ዘዴ አመድ ያደርጉታል፡፡ ጠላት እየቀረበ ሲሄድ የጀግንት ዘፈናቸውን እየዘፈኑ ሁሉም ወደ ታንኩ ይሮጣሉ፡፡ ታንኩ ምንም ማምለጫ መንገድ የለውም፡፡ ጥይት እየዘነበባቸው አንደኛው ሲወድቅ አንደኛው እየተተካ የጠላትን ጉሮሮ ያንቁታል፡፡ አንቀውም ይጥሉታል ብለዋል ኮሎኔል አልኸንድሮ፡፡
ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በመስዋዕትነታቸው ነጻነት ያደመቃት፣ ታሪክ ያከበራት፣ ትውልድ ሁሉ የሚመካባት፣ የጥቁር ዘር ሁሉ የነጻነት ብርሃን የታየባት ምሥራቅ የሚላት፣ ጠላት ሁሉ እጅ የሚነሳላት፣ ወዳጅ ሁሉ አብዝቶ የሚወዳትና የሚመካባት፣ መድረሻ ያጣው ሁሉ የሚጠለልባት ታላቅ ሀገር አቆዩ፡፡ለትውልድም አስረከቡ፡፡ ዛሬም ከአባቶቻቸው ጀግንነትን የወረሱ ጅገኖች ሀገራቸውን ይጠብቋታል፤ ያስከብሯታል፡፡ ክብር ሁሉ ስለ ኢትዮጵያ ለሚኖሩ፣ በኢትዮጵያ ለሚኮሩ፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!