
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገራችን ኢትዮጵያ ሉአላዊነቷን ለመጋፋት ፤ ክብሯን ለመግፈፍ እና የተፈጥሮ ሀብቷን ለመዝረፍ በተለያዩ ዘመናት የመጡትን የውጭ ወራሪዎችን ተከላክላ የቆየችው በውድ ልጆቿ ክቡር መስዋዕትነት ነው።
ኢትዮጵያ የድል ቀን እንጂ ነፃ የወጣችበትን ቀን የማታከብረው በየዘመናቱ በተከፈለ የልጆቿ ውድ መስዋዕትነት ነው።
ኢትዮጵያ የጀግኖች ሀገር ነች። ጀግኖች ደግሞ ላመኑበት ነገር መስዋዕትነት ለመክፈል የቆረጡ ናቸውና ሀሌም ሲዘከሩና ሲታወሱ ይኖራሉ።
..አድዋ ዛሬ ናት አድዋ ትላንት
መቼ ተረሱና የወዳደቁት… በማለት የጀግኖችን አይረሴነት ያወሳችው ድምፃዊቷም ለሀገራቸው ሲሉ በጀግንነት የወደቁ ጀግኖች ሲዘከሩ እንደሚኖሩ ለማሳየት ነው።
የመስዋዕትነት ቀን ሲዘከር በየዘመኑ ለሀገራቸው ክብርና ሉአላዊነት በክብር የወደቁት እያሰብን ብቻ ሳይሆን ዘመኑ የሚጠይቀውን መስዋዕትነትም ለመክፈል የተዘጋጁ እልፍ ጀግኖች በፅናት መቆማቸውን በተግባር በታየበት ወቅት ላይ ሆነን ነው፡፡
የዘመኑም ትውልድ ለሀገሩ ያለውን ፍቅርና ክብር በተግባር አረጋግጧል፡፡
ለሀገር ሰላም አንድነትና ክብር ከጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን ጎን በመሰለፍ መላው ህዝባችን ያደረገውና እያደረገው የሚገኘው ድጋፍም የመስዋዕትነቱ አካል ነው፡፡
ሀገራችንን ለማፍረስ ካልሆነም ደካማ የሆነች ሀገር እንድትሆን ቀን ከሌት የሚሰሩ ጠላቶች ትላንትም ነበሩ። ዛሬም አሉ፡፡ በሚጠብቋት ፤ በሚወዷትና በሚሰዉላት ልጆቿ ጥረት ድካማቸው መና ፤ ህልማቸው ቅዠት ቢሆንም እንኳ!!
የሀገራችንን ታሪክ መለስ ብለን ስናጤነው ከወራሪዎች ባልተናነሰ የግል ጥቅማቸውና ፖለቲካዊ ፍላጎታቸው ለማሳካት በሀገር ላይ የሚቆምሩ ጥቅመኞችን ጨምሮ የውጭ ጠላቶችን ፍላጎት ለማሳካት የተሰለፉ ባንዳዎች በተደጋጋሚ አጋጥመዋል።
እስከ መስዋዕትነት በመታመን ሀገሩን ከሚጠብቀው ሰላም ወዳዱ የሀገራችን ህዝብ የወጣው ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን ዛሬም የሀገሩን ሉአላዊነትና ህልውና ለማፅናት በተሟላ ቁመና መገኘቱ ከንቱ ህልማቸውን አምክኖታል እንጂ !!
በልቦናው ሀገሩን ተሸክሞ መኖር ብቻ ሳይሆን ለሚሰዋው ጀግናው ሰራዊታችን ከአለም አቀፍ ተቋማትና ከተለያዩ ሀገራት ሕዝቦች ያገኘው ፍቅርና ክብር የመስዋዕትነቱ ውጤት ነው። ሰላም ለራቃቸው የቅርብና የሩቅ ሀገራት ያመጣው ተስፋ በግልፅ የሚታይ ነውና!
ለሕዝቦች ሰላም በተሰለፈባቸው ሀገራትም የሰራዊታችን መስዋዕትነትን የሀገራችንን ታላቅነት የሚያወሱ ማስታወሻዎች በክብር ተቀምጠዋል፡፡
ሠራዊታችን ከተባበሩት መንግስታት እና ከአፍሪካ ህብረት በተደጋጋሚ የተሰጠው ሽልማት ፤ በደቡብ ኮሪያ የቆመለት ሀውልት ፤ ከላይቤሪያ ፤ ከሩዋንዳ እና ብሩንዲ ሕዝብና መንግስት የተሰጡት ሽልማቶች ከሀገራችን ባለፈ ሰላም ላጡ ሕዝቦች በመስዋዕትነቱ ያመጣውን ውጤት የሚያወሳ ቋሚ ምስክር ነው።
በሱዳን እና በሶማሊያ የሚገኙ ሕዝቦችም ሰራዊታችን በከፈለውና እየከፈለው በሚገኘው መስዋዕትነት ላገኙት ሰላም ምስክር ናቸውና በየሄደበት የሚሰጡት ክብርና ፍቅር የላቀ ነው፡፡
ሰራዊትና መስዋዕትነት ተለያይቶ አያውቅም፡፡ ለሀገር ህልውና ለሰው ልጆች ሰላም የሚከፈል መስዋዕትነት ደግሞ ክቡር መስዋዕትነት ነው፡፡
ጀግናው ሰራዊታችን በሀገሩ የመጡበትን ጠላቶቹ እስከ መስዋዕትነት በመፋለም አንድ ሕይወቱን ብቻ መስጠቱ ስለሚቆጨው ነው በተሰሙ ቁጥር የሚነዝር ስሜት የሚፈጥሩት ስንኞችን በየቀኑ ከልቡ የሚያዜመው
…..ኢትዮጵያ በኛ ደም ደምቃ በአፅማችን ፍላፅ ተማግራ
እንደታፈረች እንድትኖር ከዘመን ዘመን ተከብራ
ከመሞት በላይ እንሙት ደማችን ሺ ጊዜ ይፍሰስ
አየር አፈሯ ይባረክ ምን ጊዜም ስሟ ይታደስ! በማለት ታፍራና ተከብራ እንድትኖር በደሙ ያደመቃትንና በአፅሙ ፍላጻ የማገራትን ሀገሩን አፈሯ እንዲባረክ ስሟ እንዲታደስ ከመሞት በላይ ለመሞትና ደሙን በማፍሰስ በቁርጠኝነት መቆሙን የሚነግረን!!
የሀገራችንን አንድነት ፤ ሰላምና ሉአላዊነት ለመጋፋት የሚሞክሩ የውጭ ጠላቶቻችን ሆነ ቡድናዊ ፍላጎታቸውን በሀይል ለመጫን የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እየመከተ ያለና በመስዋዕትነቱ ሀገር እያፀና ያለ ጀግና የመከላከያ ሠራዊት መገንባት የተቻለውም ከአባቶቹ በወረሰው ጀግንነትና ሀገር ወዳድነት ነው።
የዘመናችን ሀገር የመጠበቅ ተልዕኮ ፈተናው ብዙ ነው!!ፍላጎታቸው በየወቅቱ የሚለዋወጡ ከጥቅማቸው ውጭ ሀገራዊ ፍቅርና የሰላም ትርጉም የማይገባቸው ከሀዲ ባንዳዎች ሰራዊቱን ባልዋለበት በማዋል የሌለውን ስም የሚሰጡ የማህበራዊ ሚዲያ አርበኞች የበዙበት ዘመን ነው።
ለሀገሩ ሉአላዊነትና ክብር ፤ ለመላው የሀገራችን ሕዝብ ሰላም ከመዋደቅ ውጭ ሌላ ፍላጎት የሌለውን ጀግና የሀገር ጠባቂ ሰራዊት የዳቦ ስም በማውጣት ስሙን ለማጉደፍ የተሰለፉት ጥቂት ባንዳዎች ከከፍታው ላይ ዝቅ የማያደርጉት ፤ የሚያጠነክሩት እንጂ ትጥቁን የሚያላሉት እንደማይሆን በተግባር ተፈትኖ አሳይቷል፡፡ እያሳየም ይገኛል።
ወቅቱ የሚጠይቀው መስዋዕትነት ሀገራችንን በዕድገት አበልፅገን ፤ የተፈጥሮ ሀብታችንን አልምተን ፤ ያሉንን ታሪካዊ ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ፀጋዎቻንን አሳድገን ለመጭው ትውልድ ምቹ የሆነች ሀገር ገንብተን ማቆየት እንጂ በየጊዜው በሚፈጠሩ አጀንዳዎች ተወጥረን ፤ በየቀኑ በሚፈለፈሉ ባልተረጋገጡና በውሸት መረጃዎች ተታለን ውዱ ጊዜያችንንና ሀብታችን ባለመሰዋት መሆን ይገባል፡፡
ወታደር ሀገር እንጂ ሰፈር የለውምና የሰፈር ጉልበተኞችን በመምከርና በማስታገስ ፤ የማህበራዊ ሚዲያ ጡረተኞችና የሩቅ አዋጊዎችን አጀንዳዎች ወደ ጎን በመተው ለሀገራችን ሰላምና ዕድገት በመጣር ዘመኑ የሚጠይቀውን አነስተኛ መስዋዕትነት መክፍል ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡
ዘላለማዊ ክብር ለሀገራችን ዕልውና እና ሉአላዊነት ፤ ለሕዝቦች ሰላም እና ዕድገት በክብር ለተሰው እና በተሰለፉበት ሙያ ሁሉ በታማኝነትና በቅንነት በማገልገል ለሀገራቸው መስዋዕትነት ለከፈሉ ሁሉ ይሁን!!
ዘላለማዊ ክብር ለጀግኖች ሰማዕታት!
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን