“በ41 ዓመታት የሕክምና አገልግሎት ሦስት ቀናት ብቻ እረፍት”

58

ባሕር ዳር: ጳጉሜን 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) 2012 ዓ.ም የጤና ሚኒስቴር “የሕይዎት ዘመን የላቀ የሙያ አገልግሎት ተሸላሚ” አድርጓቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፐብሊክ ሄልዝ ኢንስቲትዩትም በጤናው ዘርፍ ጥናት እና ምርምር ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽዖ የሜዳሊያ ተሸላሚ አድርጓቸዋል ዶክተር መኮንን አይችሉህም፡፡

ከፊታቸው ላይ የሚስተዋለው ፈገግታ እና ትህትና ዘመናቸውን ሁሉ ሐኪም ኾነው እንዳሳለፉ ከበቂ በላይ ምስክር ነው፡፡ ይኽ ሰው 41 ዓመታትን ሲያገለግሉ ምንአልባትም ሦስት ቀናት ብቻ እረፍት እንደወሰዱ ያስታውሳሉ፡፡ የ64 ዓመቱ ጎልማሳ ባለትዳር እና የሦስት ልጆች አባት እንደኾኑም አጫውተውናል፡፡ ዶክተር መኮነን በሙያቸው የኅብረተሰብ ጤና ሳይንስ ስፔሻሊቲ ሐኪም እና ኮንሰልታንት ፐብሊክ ሄልዝ ስፔሻሊስት ደረጃ ላይ የደረሱ ሐኪም ናቸው፡፡

የ9ኛ ክፍል ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ 10ኛ ክፍል ሲሸጋገሩ ለጤና ረዳትነት ተወዳድረው አለፉ፡፡ 1985 ዓ.ም ጎንደር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሕክምና ትምህርታቸውን ከማጠናቀቃቸው በፊት በጤና ረዳትነት ለሰባት ዓመታት ገደማ አገልግለዋል፡፡ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም ለምደባ ወደ ጤና ሚኒስቴር አቀኑ፡፡ ነገር ግን ያልጠበቁትም የማያውቁትም ነገር ገጠማቸው፤ ሀገሪቱ በክልል ተከፋፍላለች፡፡

ከሕክምናው ውጭ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ቀዳሚ ጉዳያቸው ስላልነበር እየተገረሙም ቢኾን ጤና ሚኒስቴር ለምደባ ሲቀርቡ አማራ ክልል ሐኪም አልጠየቀምና አዲስ አበባ ይመደባሉ ተባሉ፡፡ ከሕክምና ትምህርታቸው በፊት ያገለገሉት የጤና ረዳትነት ልምድ በቀጣሪዎቻቸው ዘንድ ሞገስን ሰጥቷቸዋልና እርሳቸውን አዲስ አበባ ማስቀረት የፈለጉ ይመስላሉ፡፡ የተማርኩት እኮ በችግር ውስጥ ኾኖ ያስተማረኝን አርሶ አደር ለማገልገል ነው ብለው ወደ ባሕር ዳር ከአንድ ጓደኛቸው ጋር ተመለሱ፡፡

ባሕር ዳር መጥተው ጤና ቢሮውን ስለምን ነው ክልሉ ሐኪም የማይፈልገው ሲሉ የጠየቁት ዶክተር መኮንን ጥያቄያቸው በቢሮው ሰዎች ዘንድ ቅቡልነትን አግኝቶ እንዲያውም ሐኪም ይመደብልን የሚለውን ደብዳቤ ይዘው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ፡፡ በዚኽ ሁሉ ውጣ ውረድ ውስጥ ግን አብረዋቸው የተማሩት ጓደኞቻቸው ቅጥር ተፈጽሞላቸው የሦስት ወራት ደመወዝ ተቀብለዋል፡፡ ጤና ሚኒስቴር ዶክተር መኮንን እና ጓደኛቸውን ለማስቀረት ፍላጎት ቢኖረውም በሐኪሞቹ ግፊት ወደ ክልሉ ተመደቡ፡፡

ዶክተር መኮንን ወደ ባሕር ዳር መጥተው ወደ ጤና ተቋማት ለምደባ ሲዘጋጁ ለመዳቢዎች አንድ ጥያቄ አቀረቡላቸው፡፡ “ሩቅ የምትሉት እና የጤና አገልግሎት ተደራሽ ያልኾነበት ቦታ የት ነው?” አሉ፡፡ አከታትለውም ሩቅ እና የጤና ባለሙያ ችግር አለበት በሚሉት ተቋም እንዲመድቧቸው ጠየቁ፡፡ በወቅቱ ሰውየው ባሕር ዳር የመቅረት እድል ነበራቸው፤ ነገር ግን አይኾንም አሉ፡፡ ገጠር ገብቼ ወገኔን በሙያየ ማገልገል አለብኝ የሚለው ጉዳይ ነቅነቅ የማይሉበት መርሃቸው ኾነ፡፡ ደቡብ ጎንደር ውስጥ አዲስ ዘመን ጤና ጣቢያ ላይ ተመደቡ፡፡

አዲስ ዘመን ጤና ጣቢያ ሐኪም ኾነው እያገለገሉ እያለ ከማይዘነጉት ጉዳይ አንዱ የወላድ እናቶች ስቃይ ነበር ይላሉ፡፡ ጠዋት ወደ ሥራ ሲገቡ ከእጃቸው የማይለይ ነገር ምንድን ነው ቢባል ፔርሙዝ ነበር፡፡ ለወሊድ ወደ ጤና ጣቢያው የመጡት እናቶች ከወለዱ በኋላ ቢያንስ ለ24 ሰዓታት በጤና ጣቢያው ይቆዩ ነበር፡፡ በቆይታቸው ከገጠር የሚመጡት እናቶች የሚቀርብላቸውን ምግብ ሲያዩ ስለሚከፉ ጠዋት ጠዋት አጥሚት አሰርተው ይዘው ይሄዱና ለወላዶቹ ይሰጣሉ፡፡ ይኽ ልምዳቸው የኋላ ኋላ ወደ ሥራ ባልደረቦቻቸው እና ባለቤታቸው ተላልፎ እነርሱም ይዘው ይሄዱ ነበር ፡፡

ዶክተር መኮንን አንድ ወቅት በሙያቸው ወደ ደብረ ታቦር ለስብሰባ ይሄዳሉ፡፡ በዚያ ስብሰባ እያሉ አንድ በጣም የሚያስደነግጥም የሚያስገርምም ነገር ይሰማሉ፡፡ የክልሉ መንግሥት ከተመደበለት የጤና በጀት ውስጥ ሳይጠቀምበት የበጀት ዓመቱ ተቃጥሎ 18 ሚሊዮን ብር ተመላሽ ኾነ ሲሉ ሰሙ፡፡ ይኽ ሰው ከክልሉ የጤና ቢሮ ሰዎች ጋር የጦፈ ግጭት ውስጥ ገቡ፡፡ “እኛ ጾማቸውን ውለው ጾማቸውን የሚያድሩ ወላዶችን እያየን እና እየተሳቀቅን እናንተ 18 ሚሊዮን ብር በጀት ተቃጥሎ ሲመለስ የት ነበራችሁ” የሚል ጥያቄ ላቀረቡት የሕይዎት ዘመን ሐኪም ምላሽ ለመስጠት ሞራሉ የነበረው ኅላፊ አልነበረም፡፡

ጤናን ከባለሙያነት እስከ መሪነት፤ ከመንግሥት ተቋም እስከ ግሉ ሴክተር ላለፉት 41 ዓመታት አገልግለውታል፡፡ በሥራ ዘመናቸው ፈቃድ ጠይቀው የወጡበት ቀን ግን ከሦስት ቀን አይበልጥም፡፡ “በ41 ዓመታት የሕክምና አገልግሎት ሦስት ቀናት ብቻ እረፍት” እጅግ የተለየ ቀናነት ነው፡፡ በኅላፊነት ዘመናቸው በርካታ የጤና ተቋማትን በጥረታቸው አስገንብተዋል፡፡ ከዩኒሴፍ ጋር ተጻጽፈው እና ተወያይተው ለሕጻናት የአልሚ ምግብ ማምረቻ ፍብሪካ እንዲገነባ አድርገዋል፡፡

ጋንቢ ሕክምናና ቢዝነስ ኮሌጅን ከመሰረቱት አምስት የሕክምና ባለሙያዎች መካከል አንዱ ሲኾኑ ሥራ አሥኪያጅ በመኾንም አገልግለዋል ዶክተር መኮንን፡፡ በክልሉ ያለው የግሉ ጤና ዘርፍ በተሻለ ደረጃ አገልግሎት እንዲሰጥ የድርሻቸውን ተወጥተዋል፡፡ ለ41 ዓመታት በጤናው ዘርፍ ያደረጉትን የላቀ አበርክቶ ያየው ጤና ሚኒስቴርም በ2012 ዓ.ም የላቀ የሙያ ዘርፍ ተሸላሚ አድርጓቸዋል፡፡

በሕክምና ሙያው ዘርፍ በጥናት እና ምርምር ሥራዎች ላይ አሻራቸው ያልነጠፈው ዶክተር መኮንን በበርካታ የጥናት እና ምርምር ሥራዎቻቸው በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ የመታተም እድል አግኝተዋል፡፡ ለዚህ ላቅ ያለው የሕይዎት ዘመን አበርክቷቸው የኢትዮጵያ ፐብሊክ ሄልዝ ኢንስቲትዩት ዕውቅና እና የክብር ሜዳሊያ አበርክቶላቸዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን “በሕክምና ሙያ ሥራየ ያጋጠሙኝን ውጣ ውረዶች፤ ከፍና ዝቆች በገንዘብ መተመን አልፈልግም” ይላሉ፡፡ እኛም ዶክተር መኮንን አይችሉህምን በአገላጋይነት ቀን ላይ መልካም እና ቅን አገልጋይ ብለናቸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ለፍትሕ ቢሮ አገልጋይነት መመረጥ ፍትሕ በመነፈጋቸው የተቸገሩ ሰዎችን እንባ በመልካም አገልግሎት የማበስ እድል ማግኘት ነው” የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም
Next articleጳጉሜን 2 የመስዋዕትነት ቀን በተለያዩ መርሐ ግብሮች ዛሬ ይከበራል።