
ባሕር ዳር: ጳጉሜ 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም እና የቀድሞው ቢሮ ኀላፊ አቶ ገረመው ገብረ ጻዲቅ የተቋሙ ሠራተኞች በተገኙበት መድረክ የሥራ ርክክብ አድርገዋል።
“ፍትሕ ቢሮ የሙያ ቤት ነው” ያሉት የቀድሞው ቢሮ ኀላፊ አቶ ገረመው ባለሙያን አቀናጅቶ መምራት የላቀ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ብለዋል። የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ፍትሕና ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ በርካታ የለውጥ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱንም አንስተዋል። በተለይም ባለፉት ዓመታት በርካታ ፈተናዎች ቢኖሩም ተቋሙ እና ባለሙያዎቹ ሥራቸውን በነጻነት እንዲያከናውኑ የሚያስችሉ ለውጦች መመዝገባቸውን ተናግረዋል። በየወረዳው ለሚገኙ አቃቢያን ሕግ እና ለድጋፍ ሰጭ ባለሙያዎች የትምሕርት እድል በማመቻቸት ሕዝብን በዕውቀት ለማገልገል በትኩረት ሲሠራ መቆየቱንም አቶ ገረመው ተናግረዋል።
አሁን ላይ የቢሮው ኀላፊ ኾነው የተሾሙት አቶ ብርሃኑ ጎሽም በሙያው ልምድ ያላቸው በመኾናቸው ሕዝብን የሚያረካ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላቸዋል ሲሉም ተናግረዋል። አቶ ገረመው ለአዲሱ ቢሮ ኀላፊ መልካም የሥራ ዘመንም ተመኝተው የሥራ ርክክብ አድርገዋል።
የፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ኾነው የተሾሙት አቶ ብርሃኑ ጎሽም “ለፍትሕ ቢሮ አገልጋይነት መመረጥ ፍትሕ በመነፈጋቸው የተቸገሩ ሰዎችን እንባ በመልካም አገልግሎት የማበስ እድል ማግኘት ነው” ብለዋል። ፍትሕን ተነፍገው ለሚጉላሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተቀላጠፈ ሙያዊ አገልግሎት በመስጠት ፍትሕ እና ፍትሐዊነትን ለማስፈን በትኩረት እንሠራለን ሲሉም ተናግረዋል።
አቶ ብርሃኑ በትክክልም ፍትሕ እንዲሰፍን እንደ ተቋም በዕውቀት እና በሥነ ምግባር የተመሰገኑ ባለሙያዎችን ማፍራት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል። የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ሥራዎችን በእቅድ እና በጠንካራ ክትትል የሚፈጽም እንዲኾን በትኩረት እንደሚሠሩም ቢሮ ኀላፊው ገልጸዋል። በተለይም ሕዝብን በፍትሕ እጦት ችግር ያማረሩ ጉዳዮችን በመለየት ለተሻለ ሥራ እንቀሳቀሳለን ነው ያሉት።
በጥብቅ ሥነ ምግባር የሚመራ እና ፈጣን የፍትሕ ሥርዓት በመገንባት በፍትሕ እጦት ችግር የተማረሩ ዜጎችን መካስ ተቀዳሚ ሥራችን ይኾናል ነው ያሉት አቶ ብርሃኑ።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!