“ጊዜው ከመቸውም በላይ ካለፉት ክፍተቶች በመማር ለቀጣይ ጠንክሮ መሥራትን የሚጠይቅ ነው ” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ

50

ባሕር ዳር: ጳጉሜ 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የ2016 ዓ.ም እቅዱን ገምግሟል። በግምገማ መድረኩ የ2015 ዓ.ም እቅድ አፈጻጸምንና የ2016 ዓ.ም እቅድ ያቀረቡት በአማራ ክልል ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ አቶ አየን ብርሃን ናቸው፡፡ የባለፈው ዓመት ለምክር ቤቱ የቀረቡለትን ሕግ የማውጣትና ማጽደቅ ፤ ታትመውም እንዲሰራጩ በማድረግ በኩል አበረታች ውጤት የታየበት ነበር ብለዋል።

በክትትልና ቁጥጥር ተግባሩም የቋሚ ኮሚቴ አባላት የተቋማትን ቁጥጥር እና ክትትል ሥራ ከበፊቱ በተሻለ ደረጃ ተሰርቷል ብለዋል። በዓመቱ መጨረሻ የገጠመው የሰላምና ፀጥታ ችግር ግን ተግዳሮት እንደነበርም አንስተዋል።

ውክልናን በመወጣት በኩል የምክር ቤት አባላት ሕዝቡን ታች ድረስ ወርደው የማወያየት ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት። ምክር ቤቱ ከተሰጠው የሕዝብ ውክልናን መወጣት ፤ ሕግ ከማውጣትና የተቋማትን ክትትልና ቁጥጥር ተልእኮው አንጻር በጥቅል ሲታይ ግን ክፍተቶች እንደነበሩ ነው ያነሱት።

ካለፈው ትምህርት በመውሰድ ምክር ቤቱ በ2016 ዓ.ም የሕዝብን ጥያቄ መነሻ በማድረግ በክትትልና ቁጥጥር ሥራው ጠንክሮ ለመሥራት አቅዷል ነው ያሉት። ለአማራ ክልል የሰላም እጦት መነሻ ምክንያቶች በርካታ ናቸው ያሉት አቶ አየን ብርሃን የማንነት ጉዳይ እና በውስጣዊ ችግርም የመልካም አሥተዳደር መኖር በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።

ምክርቤቱ ለሰላም እጦትና ለግጭት ምክንያት የኾኑ ጉዳዮች ላይ በሚናው ልክ መሥራት የሚያስችሉ ተግባራትን ለመፈጸም ማቀዱንም ነው የተናገሩት። መታገል የሚቻለው ግን ከሕዝብ ጋር በመኾን ነውና ሕዝቡ ለሰላምና ፍትሕ መቆም እንደሚገባ ነው የጠቀሱት።

ችግሮችን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ለችግሩ መባባ ምክንያት መኾን መልሶ የሚጎዳው ሕዝብ መኾኑን መገንዘብ ይገባል ብለዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች እንደተናገሩት ምክር ቤቱ ተልእኮውን መወጣት አለበት። በክትትልና ቁጥጥር ሥራውም በየተቋማቱ በታማኝነት የሚያገልገል ሠራተኛ እንዲፈጠር ፣ በኀላፊነት ልክም ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ የሚያስችሉ እርምጃዎች ያስፈልጋሉ ነው ያሉት።

በምክር ቤቱ መመሰጋገን እንዳለ ሁሉ መወቃቀስም ሊለመድ ይገባል ፤ ጉድለቶቻችን የሚሞላ ግምገማ ያስፈልገናል ነው ያሉት ተሳታፊዎቹ። በተቀመጠው የሥራ መገምገሚያ ሥርዓት መሰረት መገማገም እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።

“ጊዜው ከመቼውም በላይ ካለፉት ክፍተቶች በመማር ለቀጣይ ጠንክሮ መሥራትን የሚጠይቅ ነው ” ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ናቸው። ምክር ቤቱ ተልእኮውን በሚገባ ለመወጣት ሁሉም ኀላፊነቱን መወጣት እንደሚገባውም አሳስበዋል። ምክር ቤቱ የመንግሥት ተቋማት ሕዝብን የሚያማርሩ የአገልግሎት አሰጣጥን እንዲሻሽሉ ፤ ሕዝብን ከመንግሥት የሚነጥሉ የሰላምና ፀጥታ ችግሮችን ለመታገል እንደሚሠራም ነው የተናገሩት።

በቀጣይ በጀት ዓመት ምክር ቤቱ ሕዝብን እያወያየ፣ ሕዝብን ይዞ ለሰላም በትኩረት እንደሚሠራም ተገልጿል። ጠንካራ ምክር ቤት በመገንባት ያደሩ ሥራዎችን ማጠናቀቅ ፤ በቀጣይም ለሕዝብ ሰላምና እድገት ተገቢውን ውክልና ለመውጣት ይሠራል ብለዋል፡፡ የሕዝብን ቅሬታ በተገቢው መንገድ አድምጦ መፍታት እንዲቻል እንደሚሠራም ተገልጿል።

ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች በወቅታዊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራት አፈጻጸምና የቀጣይ አቅጣጫ ላይ ምክክር አደረጉ።
Next article“ለፍትሕ ቢሮ አገልጋይነት መመረጥ ፍትሕ በመነፈጋቸው የተቸገሩ ሰዎችን እንባ በመልካም አገልግሎት የማበስ እድል ማግኘት ነው” የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም