
ባሕር ዳር ጥር 7/2012ዓ.ም (አብመድ) ሆቴሎችና አስጎብኚ ድርጅቶች ለጥምቀት በዓል የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ተዘጋጅተዋል፡፡
ለእንግዶች አቀባበል ያደረጉትን ዝግጅት በተመለከተ አብመድ በባሕር ዳር ከተማ አስተዳድር የሚገኙ የሆቴል ሥራ አስኪያጅ እና አስጎብኚ ድርጅቶችን አነጋግሯል፡፡ የዩኒሰን ሆቴል ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ አክሊሉ ባለፈው የልደት በዓል ጥሩ ዝግጅት እና አፈጻጸም እንደነበራቸው ተናግረዋል፡፡ ለጥምቀትም ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሃገር ለሚመጡ እንግዶች እንደየ ባህላቸው አገልግሎት ለመስጠት ሆቴሉ በቂ ዝግጅት አድርጓል ነው ያሉት፡፡
የባሕር ዳር ከተማ የአስጎብኚዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ማስተዋል ዘለቀ ደግሞ ለጥምቀት በዓል የበጎ ፈቃድ አግልግሎት የሚሰጡ 28 ወጣቶች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡ የጎንደርን የጥምቀት በዓል ለመታደም የሚመጡ እንግዶች በባሕር ዳር የሚኖራቸውን ቆይታ ያማረ እና አይረሴ ለማድረግ ማኅበሩ መዘጋጀቱንም ነው የተናገሩት፡፡ ከዝግጅቶች መካከልም ጥር 14/2012 ዓ.ም በጣና ሐይቅ ላይ የሚካሄደው የጀልባ ትዕይንት ይጠቀሳል፡፡
የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ ወደ ባሕር ዳር ለሚመጡ እንግዶች ቀልጣፋ እና ምቹ አገልግሎት ለመስጠት በሁሉም ዘርፍ ዝግጅት መደረጉን ያስታወቀው ደግሞ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ነው፡፡ በመምሪያው የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ባለሙያ አቶ አትርሳው ዓለም በከተማ አስተዳደሩ 30 በኮኮብ ደረጃ የሚገመቱ ሆቴሎች እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት ማድረጋቸውን አረጋግጠናል ብለዋል፡፡ ከሀገር ውስጥ እና ከባሕር ማዶ ለጉብኝት የሚመጡ እንግዶች በቆይታቸው ፈጣን እና ምቹ አገልግሎት እንዲያገኙም እየተሠራ ነው፡፡
ቱሪዝሙ ለባለሆቴሎች እና በዘርፉ ለተሰማሩት ዜጎች የገቢ ምንጭ እንዲሆን መምሪያው እየሠራ መሆኑንም ባለሙያው ተናግረዋል፡፡
እንግዶች ከሆቴሎች ዘመናዊ አግልግሎት እንዲያገኙ ታሳቢ በማድረግ ቀደም ብሎ ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት ጋር ቅንጅት በመፍጠር ስልጠና እንዲሰጥ መደረጉንም አብራርተዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከሀገር ውስጥ 36 ሺህ 301 እና ከውጭ ሃገር 6 ሺህ 171 ጎብኝዎች ወደ ባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ለጉብኝት መምጣታቸውን ከከተማ አስተዳደሩ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ፎቶ፡- ከድረ ገጽ