
ባሕር ዳር: ጳጉሜ 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የ2016 ዓ.ም እቅድ ገምግሟል፡፡ ጽሕፈት ቤቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ያለውን ጳጉሜ 1 የአገልጋይነት ቀንን አስመልክቶም ወይይት አካሂዷል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ እንዳሉት በየተቋሙ ዜጎች በአገልግሎት እጦትና እንግልት እየደረሰባቸው ነው፡፡ ይህም በመንግሥትና በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ እምነት እንዳይኖራቸው ምክንያት ኾኗል ብለዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ጳጉሜ 1 የአገልጋይነት ቀን በሚል መሰየሙ ሁላችንም በሚጠበቅብንና በሚገባን ልክ በታማኝነት፣ በቅንነትና በኀላፊነት ስሜት ሕዝብን ለማገልገል የማንቂያ ማስታወሻ የሚኾን ነው ብለዋል።
“ኢትዮጵያን እናገልግል ” በሚል መሪ መልዕክት ቀኑ መከበሩ የነበረንን ጠንካራ ጎን የምናስቀጥልበት፣ ክፍተቶቻችን ለመሙላት ታልሞ የተሰየመ ስለመኾኑም አብራርተዋል።
“የአገልጋይነት ቀንን ስናከብር በተግባር ማረጋገጥ ይገባል” ያሉት አፈጉ ጉባኤዋ ዜጎች በየተቋማቱ በአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለምሬት እየተዳረጉ ነው ብለዋል። አሁን ለገባንበት የሰላም እጦትና ግጭት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ምክንያት ነውና በፍጹም ቅን አገልጋይነት ለገጠመን ወቅታዊ የሰላም እጦትና አለመረጋጋት የመፍትሔ አካል መኾን ይገባናል ብለዋል።
ለችግሩ መፈጠር ለአንድ አካል የሚተው አይደለም ያሉት አፈ ጉባኤዋ እያንዳንዱ ሰው በተሰለፈበት ሙያና ኀላፊነት ለላቀ አገልግሎት መዘጋጀት ይገባዋል ብለዋል። ለቀጣይ ስኬታማ አገልግሎትም ያለፈውን ሥህተት አርሞ ለቀጣይም መማሪያ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። የጋራ ሀገረንና አካባቢን ሰላም ለማድረግ ዜጎች በአግባቡ የመገልገል መብቶቻቸውን እንዲያረጋግጡ ማስቻል ይገባል ብለዋል።
የምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ሠራተኞችም በየተሰለፉበት የሥራ መስክ ከቀደመው በተሻለ በታማኝነትና በትጋት ሕዝብን እንደሚያገለግሉ ነው የተናገሩት ።
የተቋሙ እቅድ እንዲሳካ ፣ ለሕዝብና ሀገር ሰላም እንዲረጋገጥም በተሰጠን ሚና ልክ እንሠራለን ፤ በአገልጋይነት መንፈስም መልካም አሻራችን እናሳርፋለን ነው ያሉት አፈጉባኤ ፋንቱ ተሰፋዬ።
የመንግሥት ሠራተኛ ማለት የሕዝብ አገልጋይ ማለት ቢኾንም ተግባሩ ግን በልኩ አይደለም የሚሉት የተቋሙ ሠራተኞች ተጠያቂነት ያለበት አሠራር መዘርጋት አለበት ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!