
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳዳር በማኅበራት ተደራጅተው የቤት መሥሪያ ቦታ ላገኙ ማኅበራት በጥቂት ቀናት ውስጥ የሊዝ ውል እና አጠቃላይ ካርታ ሠርቶ ለማጠቃለል እየሠራ መኾኑን አስታውቋል፡፡
አርሶ አደር ሁነኛው ደጀን በዘንዘልማ ቀበሌ የልማት ተነሺ ናቸው፡፡ መሬታቸው ለቤት ፈላጊዎች በመፈለጉ የቤት መሥሪያ ቦታ ተፈቅዶላቸውና ካሳ ተከፍሏቸው ቤታቸውን አፍርሰው ተነስተዋል፡፡ ነገር ግን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳዳር ከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ የሊዝ ውል እና አጠቃላይ ካርታ ባለመሥጠቱ ቤታቸውን መገንባት አልቻሉም ነበር፡፡
አሁን ከተማ አሥተዳደሩ የቤት መሥሪያ ቦታ ላገኙ ማኅበራት የሊዝ ውል እና አጠቃላይ ካርታ ለመሥራት ባደረገው ርብርብ ከሌሎች ማኅበራት ጋር የሊዝ ውል እና አጠቃላይ ካርታ እየተሠራላቸው በመኾኑ ደስተኛ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡ በአፋጣኝ የግንባታ ፍቃድ እና ካርታ እንዲሠጣቸው እና ሠርተው ወደ ቤታቸው እንዲገቡም ጠይቀዋል፡፡
በከተማ አሥተዳደሩ ከተደራጁ ማኅበራት ውስጥ የውሉደ ሥላሴ ቤተብርሃን የቤት ማኅበር ሰብሳቢ አቶ መሠረት በሪሁን በ2014 ዓ.ም ቦታ መሠጠታቸውን ተናግረዋል፡፡ የሊዝ ግዴታ ለመፈረም እና የጋራ ካርታ ለመውሰድ በመምሪያው መገኘታቸውን ነግረውናል፡፡ አቶ መሠረት በመምሪያው ያገኙት አገልግሎት የተሻለ እንደኾነ ጠቁመዋል፡፡ አቶ መሠረት ዛሬ ከሚሠጠው ካርታ በተጨማሪ የግንባታ ፈቃድ በአፋጣኝ እንዲሠጥ እና ወደ ግንባታ እንዲገቡ ጠይቀዋል፡፡
የሊዝ ውል እና አጠቃላይ ካርታ መሠጠቱ ጥሩ ነው የሚሉት አቶ መሠረት የማኅበር አባላቱ በቤት ኪራይ እንግልት እየደረሰባቸው በመኾኑ ይህን ችግር ሊፈታ የሚችል ምላሽ እንደሚጠብቁም ጠቁመዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ የከተማ ልማት ዘርፍ ምክትል ሥራ አሥኪያጅ ዳዊት የኔው በ2013 /14 ዓ.ም ተደራጅተው በ2015 ዓ.ም የብሎክ ቁጥር የወሰዱ የዘንዘልማ እና የመሸንቲ ማኅበራት የሊዝ ውል እና አጠቃላይ ካርታ ለመሥጠት እየሠሩ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ኮሚቴ እንዲጣራ በወሰነው መሠረት ማግኘት ያለባቸው አባላት ተጣርቶ መድረሱንም ተናግረዋል፡፡
አቶ ዳዊት ለተደራጁ ቤት ፈላጊዎች በዘንዘልማ ሳይት 570 ሄክታር በላይ መሬት በመሸንቲ ሳይት 220 ሄክታር መሬት ተዘጋጅቶ ለማኅበራት መሰጠቱን አንስተዋል፡፡
ምክትል ሥራ አሥኪያጁ እንዳሉት የተገልጋዮችን እንግልት በመቀነስ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመሥጠት የመምሪያው ሠራተኞች ሥራውን በዕቅድ ለመሥራት ባወጡት የማስፈጸሚያ ዕቅድ አምስት ቡድን ተደራጅቶ እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
የመምሪያው ሠራተኞች በተግባቡት መሠረት ሥራው ፍጻሜ እንዲያገኝ እየሠሩ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡
አቶ ዳዊት በዘንዘልማ ሳይት ከተደራጁ 699 ማኅበራት ውስጥ ለ510 ማኅበር ፤ከተነሺ አርሶ አደር ልጆች ከ216 ማኅበር ለ193 ማኅበር በወጣው ቅደም ተከተል መሠረት የሊዝ ውል እና አጠቃላይ ካርታ እንደሚሠጣቸው ተናግረዋል፡፡
በዘንዘልማ ሳይት የሊዝ ውል እና አጠቃላይ ካርታ የሚወስዱ ማኅበራት ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ መሸንቲ በመዞር እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
አቶ ዳዊት ማኅበራት በወጣላቸው ጊዜ መጥተው አጠቃላይ ካርታ በማውጣት ውል ወስደው ወደ ሥራ እንዲገቡም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ሠራተኞች ባደረጉት ርብርብ ሥራው በጥቂት ቀን እንደሚጠናቀቅም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡-ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
